ሩሲያ፤ ኔቶ ጦር ወደ ዩክሬን የሚልክ ከሆነ ቀጥተኛ ግጭት ይፈጠራል ስትል አስጠነቀቀች
የዩክሬኑ ጦርነት ከ1962ቱ የኩባ የሚሳይል ቀውስ ወዲህ በአሜሪካ እና በምዕራባውያን መካከል ከባድ ውጥረትን ፈጥሯል
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን በትናንትናው እለት የአውሮፓ ሀገራት ጦራቸውን ወደ ዩክሬን ሊልኩ እንደሚችሉ ተናግረው ነበር
ሩሲያ፤ ኔቶ ጦር ወደ ዩክሬን የሚልክ ከሆነ ቀጥተኛ ግጭት ይፈጠራል ስትል አስጠነቀቀች።
ሩሲያ አውሮፓውያን የኔቶ አባል ሀገራት በዩክሬን ለመዋጋት ጦር የሚልኩ ከሆነ በአሜሪካ በሚመራው ኔቶ እና በሩሲያ መካከል ግጭት መፈጠሩ የማይቀር ነው ስትል በዛሬው እለት አስጠንቅቃለች።
የዩክሬኑ ጦርነት ከ1962ቱ የኩባ የሚሳይል ቀውስ ወዲህ በአሜሪካ እና በምዕራባውያን መካከል ከባድ ውጥረትን ፈጥሯል።
ፕሬዝደንት ፑቲንም ቀደም ሲል በኔቶ እና በሩሲያ መካከል የሚደረግ ቀጥተኛ ግጭት አደጋው የከፋ ይሆናል ሲሉ አስጠንቅቀው ነበር።
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን በትናንትናው እለት የአውሮፓ ሀገራት ጦራቸውን ወደ ዩክሬን እንዲልኩ በር ከፍተዋል። ነገርግን በሀገራቱ በጉዳዩ ላይ ከስምምነት አለመድረሳቸውን ማክሮን ተናግረዋል።
ስለማክሮን አስተያየት የተጠየቁት የሩሲያ ቤተመንግስት ክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ "የተወሰነ ኃይል ወደ ዩክሬን ለመላክ ስለሚቻልበት ሁኔታ ውይይት መደረጉ አዲስ እና ጠቃሚ ነገር ነው" ብለዋል።
ፔስኮ ኔቶ ጦር ቢልክ ሊፈጠር ስለሚችለው አደጋ ተጠይቀው "እንደዚያ ከሆነ የምናወራው ግጭት ሊከሰት ይችላል ስለሚለው ሳይሆን ስለግጭቱ አይቀሬነት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
ሩሲያ በፈረንጆች 2022 በዩክሬን ላይ ልዩ ያለችውን ወታደራዊ ዘመቻ ከከፈተች በኋላ ምዕራባውን ሀገራት ዩክሬን ሩሲያን እንድታሸንፍ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ሲገልጹ ቆይተዋል።ነገርግን ያ እስካሁን አልሆነም።
ዩክሬን በፈረንጆቹ 2023 የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ የከፈተች ቢሆንም የሩሲያ ምሽግ መስበር አልተሳካላትም።
ሩሲያ በአንጻሩ በምስራቅ ዩክሬን በርካታ ቦታዎችን እየተቆጣጠረች ትገኛለች።
ማክሮን 1/5 ኛውን የዩክሬን ግዛት የያዘችውን ሩሲያን ለማሸነፍ ምዕራባውያን የትኛውንም አማራጭ ሊጠቀሙ ይችላሉ ብለዋል።