ምዕራባውያን ለዩክሬን ወታደሮችን በመላክ እቅድ ዙሪያ ምን አቋም አላቸው?
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን "ሩሲያ እንዳታሸንፍ የትኛውንም እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል" ብለዋል
ኬቭ በበኩሏ ምዕራባዊያን የገቡትን የድጋፍ ቃል በሚገባ እየፈፀሙ አይደለም ስትል ወቅሳለች
ምዕራባውያን ወደ ዩክሬን ወታደሮችን የመላካቸው ጉዳይ "ከውሳኔ ተደርሶበት የተዘጋ" አይደለም አሉ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን።
በዩክሬን ጉዳይ ለመምከር በፓሪስ ለተሰባሰቡ የአውሮፓ ሀገራት መሪዎች ንግግር ያደረጉት ማክሮን እግረኛ ጦር የመላክ እቅዱ እስካሁን ስምምነት ላይ ባይደረስበትም ከአማራጮች ዝርዝር የሚወጣ ግን አይደለም ብለዋል።
"የሩሲያ መሸነፍ ለአውሮፓ ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ ነው" ያሉት ፕሬዝዳንቱ፥ ለዚህም ወታደሮችን መላክን ጨምሮ የትኛውንም እርምጃ መውሰድ ተገቢ መሆኑን አብራርተዋል።
ማክሮን ወደ ዩክሬን ወታደሮችን በመላክ ጉዳይ የሀገራቸውን አቋም ለማንፀባረቅ ግን አልፈለጉም ብሏል ፍራንስ 24 በዘገባው።
በዩክሬን ድል እየቀናት የምትገኘው ሩሲያ በሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ጦርነት ልትከፍት ትችላለች የሚል ስጋት ተፈጥሯል።
በተለይ የዩክሬን አጋር የሆኑት ኢስቶኒያ፣ ላቲቪያ፣ ሉቲኒያ እና ፖላንድ የሞስኮ ወረራ ስጋት ውስጥ የከተታቸው ሀገራት ናቸው።
በፓሪሱ ጉባኤ ላይ የተገኙት የሰሎቫኪያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሮበርት ፊኮ፥ የተወሰኑ የአውሮፓ ህብረትና የኔቶ አባል ሀገራት ወታደሮችን የመላኩን እቅድ ይደግፉታል ብለዋል፤ ሀገራቱን ግን አልጠቀሱም።
በጉባኤው ላይ የተሳተፉት የጀርመን እና ፖላንድ መሪዎችም ወታደሮችን ስለመላክ ሀሳብ አለመስጠታቸው ነው የተገለፀው።
በፓሪሱ ጉባኤ መሪዎቻቸውን ያላሳተፉት አሜሪካና ብሪታንያም ወታደሮቻቸውን ወደ ኬቭ መላክ ጦርነቱን አድማሱን ያሰፋዋል የሚል ስጋት እንዳላቸው አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
መዘግየታችን ዋጋ አስከፍሎናል ያሉት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት የአውሮፓ ሀገራት ለዩክሬን ሚሳኤሎችና ቦምቦችን በጥምረት የሚያቀርቡበት ስርአት በቅርቡ ይፋ ይደረጋል ብለዋል።
ሀገራቱ ከኬቭ ጋር በመተባበር የጦር መሳሪያዎችን በፍጥነትና ብዛት እንዲያመርቱ ከስምምነት ላይ መደረሱንም ነው ያነሱት።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ በቪዲዬ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የምዕራባውያን የጦር መሳሪያ ድጋፍ በጊዜ አለመድረስ በጦርነቱ ላይ ያሳረፈውን ተፅዕኖ አብራርተዋል።
ዩክሬን ከአውሮፓ ሀገራት ቃል ከተገባላት የጦር መሳሪያ ድጋፍ የደረሳት 30 በመቶው ብቻ መሆኑንም በመጥቀስ።
የዩክሬን መከላከያ ሚኒስትር ሩስተም ኡሜሮቭም ከምዕራባውያን ድጋፍ ከግማሽ በላዩ ኬቭ የደረሰው በጣም ዘግይቶ ነው ማለታቸው ተዘግቧል።