የሩሲያን ወታደራዊ አቅም ዝቅ አድርጎ መመልከት ስህተት መሆኑን ኔቶ አሳሰበ
ከሩሲያ ጋር የመደራደሩን ጉዳይ ዩክሬን በራሷ መንገድ ልትወስን እንደሚገባም ተገልጿል
የሩሲያ ጦር አሁንም የመዋጋት አቅሙ እና በተዋጊ ወታደሮቹ ብዛት ስጋት መሆኑ መዘንጋት የለበትም ተብሏል
የሩሲያን ወታደራዊ አቅም ዝቅ አድርጎ መመልከት እንደማይገባ ኔቶ አሳሰበ።
የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶ ዋና ጸሀፊ ጀንስ ስቶልትንበርግ በኔዘርላንድ በሰጡት መግለጫ ላይ እንዳሉት ዩክሬን በሩሲያ ጦር የተያዙ ቦታዎችን በማስለቀቅ ላይ መሆኗን ተናግረዋል።
ይሄንን ተከትሎም የተለያዩ አካላት የሩሲያን ወታደራዊ አቅም አሳንሶ የመመልከት አዝማሚያ አለ የሚሉት ዋና ጸሀፊው ይህ ግን ስህተት ነው ብለዋል።
የሩሲያ ጦር አሁንም እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ቦታዎችን ተቆጣጥሮ እንዳለ እና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተዋጊ ወታደሮች እንዳሉት መዘንጋት የለበትም ተብሏል።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬንን በቀጣዮቹ ቀዝቃዛ ወራት ውስጥ ያለ ሀይል እንዲቆዩ የማድረግ እቅድ እንዳለው የተናገሩት ስቶልትንስበርግ የሞስኮ እቅድ እንዳይሳካ ለዩክሬን ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
ዋና ጸሀፊው አክለውም ከሩሲያ ጋር በሚደረገው ድርድር ላይ ጦርነቱ መቼ እና እንዴት ይጠናቀቅ በሚለው ጉዳይ ላይ ዋነኛ ወሳኝ ሀገር ዩክሬን ብቻ እንደሆነች ጠቅሰዋል።
ሩሲያ ከሁለት ወር በፊት በህዝበ ውሳኔ ወደራሷ የጠቀለለቻት ኬርሰን ግዛት ከትናንት በስቲያ በዩክሬን ወታደሮች መያዟ ይታወሳል።
ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ ነጻ የወጣችው ኬርሰን ግዛትን በጎበኙበት ወቅት እንዳሉት "ይህን ቦታ መልሰን መቆጣጠራችን የጦርነቱ መጨረሻ የመጀመሪያው ድል ነው" ብለዋል።