በኬርሶን ከ400 በላይ የጦር ወንጀሎች መፈፀማቸውን ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ገለጹ
ፕሬዚዳንቱ፤ በኬርሰን የበርካታ ንፁሃን እና ወታደሮች አስከሬን መገኘቱን ተናግረዋል
ሩሲያ ከኬርሶን ወታደሮቿን ማስወጣት ማጠናቀቋን አስታውቃለች
በኬርሰን ከ400 በላይ የጦር ወንጀሎች መፈፀማቸውን መርማሪዎች ደርሰውበታል ሲሉ የዩክሬን ፕሬዝዳን ቮልድሚር ዜለንስኪ ገለጹ።
ፕሬዚዳንቱ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት፥ በኬርሰን የበርካታ ንፁሃን እና ወታደሮች አስከሬን መገኘቱን ተናግረዋል።
የሩስያ ወታደሮች መግባት በቻሉበት የዩክሬን ከተሞች ሁሉ የፈፀሙትን አይነት አሰቃቂ ድርጊት በኬርሰንም አድርገውታል ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ዘሌንስኪ።
"ማንኛውንም ገዳይ ይዘን ለፍትህ እናቀርባለን ፤ አትጠራጠሩ" ሲሉም ዝተዋል። ፕሬዚዳንቱ መርማሪዎች ደርሰውበታል ስላሉት 400 የጦር ወንጀሎች ግን እስካሁን የወጣ ማስረጃ የለም።
ሞስኮም ተያያዥ የኬቭን ውንጀላ እንደማትቀበለው ደጋግማ መግለጿ ይታወሳል።
የዩክሬንና ሩስያ ጦርነት በየካቲት ወር መጨረሻ ከተጀመረ ወዲህ በቡቻ፣ ኢዝዩም እና ማሪዮፖልን ጨምሮ በበርካታ ከተሞች የጅምላ መቃብሮች ተገኝተዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባለፈው ወር ባወጣው መግለጫ በጦርነቱ የጦር ወንጀል መፈፀሙንና አብዛኛውን ድርሻ የሩስያ ወታደሮች ይወስዳሉ ማለቱ ይታወሳል።
በሌላ በኩል ዩክሬን በኬርሰን የስአት እላፊ አዋጅ ታውጇል።
ሩስያ ከሉሃንስክ፣ ዶኔትስክ እና ዛፓሮዢያ ጋር ኬርሰንን በመስከረም ወር የግዛቷ አካል አድርጋ ነበር።
ባለፈው ሳምንት ግን ከ30 ሺህ በላይ ወታደሮቿን ከኬርሰን ማስወጣቷን ገልፃለች። ሞስኮ ተሸንፋ ኬርሰንን ለቃ ወጥታለች ያሉ ዩክሬናውያንም አደባባይ ወጥተው ደስታቸውን ሲገልፁ ታይቷል።
ይሁን እንጂ የሩስያ ወታደሮች አሁንም ጥቃት ሊያደርሱ ይችላሉ በሚል ስጋት ነው የስአት እላፊ አዋጅ የታወጀው።
ለሩስያ ወታደሮች ድጋፍ ሲያደርጉ የቆዩ ዩክሬናውያንም ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል ፕሬዚዳንት ዜለንስኪ።
ከዚህም ባሻገር በኬርሰን የተቋረጡ የመብራትና ውሃ እንዲሁም የኢንተርኔት እና የቴሌቪዥን ስርጭትን ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ መሆኑን መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።