ኔቶ ከሩሲያ ሊቃጣ የሚችል ጥቃትን ለመከላከል ከ30 እስከ 50 ተጨማሪ ብርጌዶች እንደሚያስፈልጉት ተነገረ
ሞስኮ በዩክሬን ላይ ውግያ መክፈቷን ተከትሎ ኔቶ ከሶስት አስርተ አመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የመከላከያ እቅድ በማዘጋጀት ላይ ነው
በአሁኑ ወቅት የኔቶ አባል ሀገራት አጠቃላይ የወታደር ቁጥር ከ3.5 ሚሊየን በላይ ነው
ኔቶ ከሩሲያ ሊቃጣ የሚችል ጥቃትን ለመከላከል ከ30 እስከ 50 ተጨማሪ ብርጌዶች እንደሚያስፈልጉት ተነገረ
ሞስኮ በዩክሬን ላይ ውግያ መክፈቷን ተከትሎ ኔቶ ከሶስት አስርተ አመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የመከላከያ እቅድ በማዘጋጀት ላይ ነው።
የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ድርጅት የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነትን ተከትሎ ከሶስት አስርተ አመታት ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ የመከለከያ እቅድ እያዘጋጀ ሲሆን በዚህ ሳምንት በዋሽግተን በሚካሄደው የኔቶ አመታዊ ጉባኤ ላይ እቅዱ ይመከርበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የሶቭየት ህብረትን መስፋፋት ለመግታት በሚል በ1949 በ12 አባል ሀገራት የተመሰረተው ኔቶ 32 ሀገራትን በአባልነት ይዟል፡፡
ከቀዝቅዛቃው ጦርነት ማብቃት ከሶቭየት መፈራራስ እና ከጀርመን ግንብ መፍረስ በኋላም አይኑን ከሞስኮ ላይ ያልነቀለው ቡድን የሞስኮ እና የኬቭ ውግያ ወደ ቀጠናው አባል ሀገራት ሊስፋፋ ይችላል በሚል በስጋት ላይ ይገኛል፡፡
ጦርነቱን ተከትሎ ኔቶ ለዩክሬን ከፍተኛ ወታደራዊ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ ግጭቱ ወደ አባል ሀገራቱ ቢስፋፋ በምን አይነት መልኩ መመከት እንደሚቻል የሚሳይ እቅድ በማዘጋጀት ላይ ነው፡፡
ሮይተርስ እቅዱን ከሚያዘጋጁ አካላት አገኝሁት ባለው መረጃ መሰረት ይህ ወታደራዊ እቅድ በፖላንድ እና ጀርመን እግረኛ ወታደሮችን ማሰማራት እና የአየር መቃወሚያ ቴክኖሎጂዎችን ማጠናከር ያካትታትል፡፡
ተጨማሪ ብርጌድ እንዲዘጋጅ የቀረበው መጠን ከ35 – 50 ሲሆን አንድ ብርጌድ ከ3ሺህ እስከ 7ሺህ ወታደር ይይዛል፡፡
ተጨማሪ እንዲዋቀር የተጠየቀውን ብርጌድ አዲስ ወታደሮችን በመመልመል ወይስ ከአባል ሀገራቱ በተውጣጡ ወታደሮች ለማወቀር እንደታሰበ ግልጽ የሆነ ነገር የለም፡፡
ከሞስኮ በ1643 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኝው በርሊን በዚህ ወታደራዊ እቅድ ውስጥ ሰፊ ትኩረት ካገኙ የኔቶ አባል ሀገራት መካከል ቀዳሚዋ ናት ፡፡
በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የኔቶ ግንባር የነበረችው ጀርመን በወቅቱ ፓትሪዎት የተሰኙ 36 የአየር መቃወሚያዎች ነበሯት፤ በርሊን የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነትን ተከትሎ የአየር መከላከያዋን በአራት እጥፍ አሳድጋለች፡፡
የኔቶ ወታደራዊ ስትራቴጂስቶች አዲስ በማዘጋጀት ላይ በሚገኙት እቅድ በሩሲያ አቅርቢያ የሚገኙ አባል ሀገራት ጥቃት ቢደርስባቸው ለሚሰጠው ምላሽ የሚያስፈልጉ ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎች እና ጦር መሳርያዎች ፣
የወታደሮች ቁጥር፣ መሰረታዊ የህዝብ መስረተ ልማቶችን እና የመከላከያ ዲፖዎችን በምን አይነት መልኩ መከላከል እንደሚቻል በዚህ ሳምንት በዋሽንግተን በሚኖረው አመታዊ ጉባኤ ለአባል ሀገራቱ መሪዎች ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአሁኑ ወቅት የኔቶ አባል ሀገራት አጠቃላይ የወታደር ቁጥር 3.5 ሚሊዮን የተሻገረ ሲሆን 1.3 ሚሊዮን ጦር ያላት አሜሪካ ከስብስቡ በወታደራዊ አቅም ቀዳሚዋ ናት። በሁለተኛ ደረጃ ላይ 355ሺህ ጦር ያላት ቱርክ ትገኛለች፡፡
በአንዱ ላይ የሚደርስ ጥቃት በሁላችንም ላይ እንደተቃጣ ይቆጠራል በሚል የተማማሉት የኔቶ አባል ሀገራት ከጥቅል ሀገራዊ ምርት እድገታቸው 2 በመቶውን ለቡድኑ ለማዋጣት ቃል ገብተዋል፡፡