ዜለንስኪ ዩክሬን ለሩሲያ ጥቃት ፈጣንና ጠንካራ የአጻፋ ምላሽ እንደምትሰጥ ዛቱ
በትናንትናው እለት በኬቭና በሌሎች የዩክሬን ከተሞች በተፈጸሙ የሚሳኤል ጥቃቶች የሟቾቹ ቁጥር 41 ደርሷል
ኔቶ ዛሬ አመታዊ ጉባኤውን ሲጀምር ለኬቭ የሚደረገውን ድጋፍ ስለማጠናከ ይመክራል ተብሏል
ዩክሬን በሩሲያ ለተፈጸመባት የሚሳኤል ጥቃት ፈጣን የአጻፋ እርምጃ እንደምትወስድ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ተናገሩ።
በትናንትናው እለት ኬቭን ጨምሮ በተለያዩ የዩክሬን ከተሞች በተፈጸሙት የሚሳኤል ጥቃቶች የሞቱ ዩክሬናውያን ቁጥር 41 ደርሷል።
በኬቭ በሚገኘው የህጻናት ሆስፒታል የደረሰውን ዘግናኝ ጥቃት የሚያሳይ ምስል ያጋሩት ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ትናንት ከፖላንድ ጋር የደህንነት ትብብር ተፈራርመዋል።
ዜለንስኪ በዚሁ ወቅት “በርግጠኝነት በእነዚህ ሰዎች ላይ (በሩሲያ) ጠንካራ የአጻፋ እርምጃ እንወስዳለን፤ ጥያቄው አጋሮቻችን ለዚህ ምላሽ ይሰጣሉ ወይ የሚለው ነው” ብለዋል።
የሰሜን ጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) በዛሬው እለት አመታዊ ጉባኤውን ትናንት በኬቭ የተፈጸሙ የሚሳኤል ጥቃቶችን በማውገዝ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።
ኬቭ በኔቶ አመታዊ ጉባኤ ከምዕራባውያን የተሰጧት የጦር መሳሪያዎች ወደ ሩሲያ ግዛት ዘልቀው በመግባት ጥቃት ማድረስ እንዲችሉ ሊፈቀድ ይገባል ነው ያሉት።
ኔቶ ይህን ውሳኔ ካላሳለፈ ዩክሬን መደብደቧን እንድትቀጥል እንደፈቀደ ይቆጠራል ማለታቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል።
የኔቶ አባል ሀገራት ለኬቭ የላኩት የጦር መሳሪያ የሩሲያን ግዛት አልፎ ገብቶ ጥቃት ካደረሰ ከሞስኮ ጋር በቀጥታ ጦርነት ውስጥ ያስገባናል የሚል ስጋት አላቸው።
ትናንት ከዩክሬን ጋር የደህንነት ስምምነት የተፈራረመችው ፖላንድም ኔቶ ከስምምነት ላይ ከደረሰ የሩሲያን ሚሳኤሎች መትቶ ለመጣል ከኬቭ ጋር በትብብር እንደምትሰራ አስታውቃለች።
ዩክሬን ከ21 ሀገራት ጋር የወታደራዊ ትብብር ስምምነት ብትፈራረምም ከሩሲያ ለተቃጣባት ጥቃት ምላሽ መስጠትም ሆነ የተነጠቁባትን ግዛቶቿን ማስመለስ አልቻለችም።
የሩሲያን ጥቃት ለመከላከል ከ35 እስከ 50 ተጨማሪ ብርጌዶች ያስፈልጉታል የተባለው ኔቶም ከ30 አመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወታደራዊ እቅድ ማዘጋጀቱ ተሰምቷል።
በፖላንድ እና ጀርመን እግረኛ ወታደሮችን ማሰማራት እና የአየር መቃወሚያ ቴክኖሎጂዎችን ማጠናከርን የሚያካትተው እቅድ ዛሬ በሚጀመረው የኔቶ አመታዊ ጉባኤ ይመከርበታል ተብሏል።