የፑቲን ዋነኛ ተቀናቃኝ አሌክሲ ናቫልኒይ እስር ቤት ውስጥ ህይወቱ አለፈ
የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን "ፑቲን እና ወንጀለኞች የሰሩት ነው" ሲሉ ፕሬዝደንት ፑቲንን ለናቫልኒይ ሞት ተጠያቂ አድርገዋል
የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ ሞቱን በተመለከተ ምዕራባውያን መሪዎች የሚያሰሙት ንግግር ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል
የፑቲን ዋነኛ ተቀናቃኝ አሌክሲ ናቫልኒይ እስር ቤት ውስጥ ህይወቱ አለፈ።
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዋነኛ ተቀናቃኝ አልክሲ ናቫልኒይ በአርክቲክ በሚገኘው እስር ቤት ውስጥ ራሱን ከሳተ በኋላ ህይወቱ ማለፉን ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
የቀድሞው የኬጂቢ ስለላ ሰራተኛ የነበሩት ፑቲን እስከ 2030 በስልጣን ለመቆየት በምርጫ ለመሳተፍ እየተዘጋጁ ባለበት ወቅት የ47ቱ የቀድሞ የህግ ባለሙያ ናቫልኒይ ሞት ለሩሲያ ተቃዋሚዎች ተሰፋ የሚያስቆርጥ ሆኖባቸዋል።
ናቫልኒይ የ30 አመት እስር ነበር የተፈረደበት።
አሜሪካ እና ምዕራባውያን ሀገራት ለናቫልኒይ ሞት ተጠያቂው ፕሬዝደንት ፑቲን ናቸው የሚል ወቀሳ እያቀረቡ ናቸው።
የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን "ፑቲን እና ወንጀለኞች የሰሩት ነው" ሲሉ ፕሬዝደንት ፑቲንን ለናቫልኒይ ሞት ተጠያቂ አድርገዋል።
ናቫልኒይ ከአስር አመት በፊት ታዋቂነትን ያተረፈው በፑቲን በምትመራው ሩሲያ የተፈጸመው ሙስናዎችን በመመዝገብ እና ተቃውሞውን በአደባባይ በማስማቱ ነበር።
ናቫልኒይ በሩሲያ ካሉ ተቃዋሚዎች ሁሉ ተጽዕኖ መፍጠር የሚችል ነው።
ከሞስኮ 1900 ኪሎሜትር በሚርቀው የያማሎ ኔንትስ ራስ ገዝ ግዛት የሚገኘው የፌደራል ፔንቲቴንሻሪ አገልግሎት ባወጣው መግለጫ ናቫልኒይ በእስር ቤቱ ውስጥ እንቅስቃሴ ካደረገ በኋላ የህመም ስሜት እንደተሰማው ገልጿል።
ናቫልኒይ ራሱን መሳቱን እና ወዲያዉኑ መሞቱን የገለጸው አገልግሎቱ የተደረገው ነፍስ የማዳን ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል ብሏል።
የናቫልኒይ ሚስት ዩሊያ በሙኒክ እየተካሄደ ባለው የጸጥታ ስብሰባ ላይ እንደተናገረችው የባለቤቷን መሞት እርግጠኛ አይደለችም።
"ፑቲን እና መንግስታቸው...ያለማቋረጥ ይዋሻሉ።"ነገርግን እውነት ከሆነ ፑቲን እና መንግስታቸው በሀገራችን፣ በቤተሰባችን እና በባለቤቴ ላይ በሰሩት እንደሚጠየቁ ማወቅ አለባቸው" ስትል ተናግራለች።
ክሬሚሊን ፑቲን የናቫልኒይ ሞት ሰምተዋል ብሏል።
የ71 አመቱ የኬጂቢ ሰላይ የነበሩት ፕሬዚዳንት ፑቲን በተራራማው ኡራል ግዛት ውስጥ በሚገኝ ፋብሪካ ውስጥ ከሰራተኞች ጋር በተደረገው ስብሰባ ላይ ታይተዋል። ፑቲን ስለናቫልኒይ በይፋ ምንም ተናግረው አያውቁም።
ናቫልኒይ የነጻነት ታጋይ ነው በማለት እየዘከሩት ያሉት ምዕራባውያን ፑቲንን በግድያ ከሰዋል፣ መጠየቅ አለባቸውም ብለዋል።
የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ ሞቱን በተመለከተ ምዕራባውያን መሪዎች የሚያሰሙት ንግግር ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል።