ክሬምሊን በበኩሉ የምዕራባውያን ውንጀላ "አሳፋሪና ፍፁም ተቀባይነት የሌለው ነው" ብሏል
ታዋቂው የሩሲያ ፖለቲከኛ፣ የፀረሙስና ታጋይ እና ጠበቃ አሌክሲ ናቫልኒ እስር ቤት ውስጥ ህይወቱ ማለፉ ተገልጿል።
የተለያዩ ሀገራት መሪዎችም የናቫልኒ ህልፈት ተፈጥሯዊ አይመስልም፤ በአስቸኳይ ምርመራ ይጀመር እያሉ ነው።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን "አልሳሳትም ለናቫልኒ ሞት ተጠያቂው ፑቲን ነው" ያሉ ሲሆን የ47 አመቱ የፑቲን ዋነኛ ተቃዋሚ እስርና ሞት እንደሚጠብቀው እያወቀ ወደ ሩሲያ መመለሱ የፅናቱ ማሳያ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
ባይደን ከሶስት አመት በፊት ናቫልኒ ሲታሰር ግለሰቡ በእስር ቤት ውስጥ የሚገደል ከሆነ ሩሲያ "ከባድ ዋጋ ትከፍላለች" ማለታቸው የሚታወስ ነው።
የአሜሪካው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማም ናቫልኒ "በጭቆና እና በደል ያልተሰበረ፤ ላመነበት ነገር ያለፍርሃት የታገለ" ነው ብለዋል።
የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክም የናቫልኒን ሞት ዜና "አስደንጋጭ" ነው ያሉ ሲሆን፥ በለንደን የሚገኙትን የሩሲያ አምባሳደር ለማብራሪያ ጠርተዋል።
የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ በበኩላቸው አሌክሲ ናቫልኒ ለነፃነትና ዴሞክራሲ ያደረገው ትግል ሁሌም ሲወሳ የሚኖር ነው ብለዋል።
ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት እንዳትከፍት ሲጠይቅ የቆየው ናቫልኒ "ያለምንም ጥርጥር በፑቲን ተገድሏል" ያሉት ደግሞ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ናቸው።
የአውሮፓ ህብረት ምክርቤት ፕሬዝዳንት ቻርለስ ሚሸል "ናቫልኒ ለእምነቱ የመጨረሻውን መስዋዕትነት ከፍሏል፤ ለህልፈቱም ብቸኛው ተጠያቂ የሩሲያ መንግስት ነው" ብለዋል።
የሩሲያ መንግስት ግን በምዕራባውያን ሀገራት እየበረበ ያለውን ክስ አይቀበለውም።
የክሬምሊን ቄል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ "የምዕራባውያን ውንጀላ አሳፋሪና ፍፁም ተቀባይነት የሌለው ነው" ማለታቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
የ47 አመቱ ፓለቲከኛ እና የፀረ ሙስና ታጋይ ህልፈት ከተሰማ በኋላ በሞስኮ እና ሴንትፒተርስበርግ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ሞክረዋል የተባሉ ከ100 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ተብሏል።
ለአምስተኛ የስልጣን ዘመን የሚፎካከሩበትን ምርጫ በቅርቡ የሚያደርጉት ቭላድሚር ፑቲን ስለናቫልኒ ሞት እስካሁን ያሉት ነገር የለም።