ፕሬዝዳንት ፑቲን ከአሜሪካና ኔቶ ጋር በአስቸኳይ መነጋገር እንደሚፈልጉ አስታወቁ
ፕሬዝዳንት ፑቲን ከፊንላንድ እና ከፈረንሳይ አቻዎቻቸው ጋር በስልክ ተወያይተዋል
ኔቶ በዩክሬን የሚያደርገውን የወታደራዊ አቅም ማስፋፋት እንዲያቆምም ሩሲያ ጠይቃለች
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሩሲያ ደህንነት ዙሪያ ከሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) እና ከአሜሪካ ጋር መነጋገር እንደሚፈልጉ አስታወቁ።
ፕሬዝዳቱ በትናንትናው እለት እንዳስታወቁት ከሆነ ከዩክሬን ጉዳይ ጋር ተያይዞ በሞስኮ እና በምእራባውያን መካከል ያለው ፍጥጫ እያየለ መምጣቱን ተከትሎ “በሩሲያ ደህንነት ዙሪያ ከአሜሪካ እና ኔቶ ጋር በአስቸኳይ መነጋገር እፈላጋለሁ” ሲሉ አስታውቀዋል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከፊንላንዱ አቻቸው ሳውሊ ኒኒስቶ በስልክ ውይይት ማድረጋቸውን ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘግቧል።
በውይይታው ወቅትም ፕርዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ፤ ሞስኮ የደህንነት ውይይቶች በአስቸኳይ እንዲጀመር ትፈልጋለች ማለታቸው ተሰምቷል።
ሞስኮ የሀገሪቱን ደህንነት ለማረጋገጥ እና ለደህንነቷ ዓለም አቀፍ ዋስትና ለማግኘት ከሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) እና ከአሜሪካ ጋር በአስቸኳይ ንግግሮችን እና ድርድሮችን የመጀመር ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) በጎረቤት ሀገር ዩክሬን የሚያደርገውን የወታደራዊ አቅም ማስፋፋት እንዲያቆምም የሩሲያ ፍላጎት መሆኑ ተነግሯል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ባደረጉት ውይይትም ተመሳሳይ ሀሳብ ማንፀባረቃቸው ተሰምቷል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ባሳለፍነው ሳምንት ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ጋር በቪዲዮ ባደረጉት ውይይት፤ በዩክሬን አቅራቢያ የሚንቀሳቀሱ የሩሲያ ወታደሮች ጥቃት ከሰነዘሩ ሞስኮ ከዚህ ቀደም ከአሜሪካ አይታው የማታውቅ ማዕቀብ ይጠብቃታል ሲሉ ተደምጠዋል።
የአውሮፓ ህብረት እና የቡድን ሰባት አባል ሀገራት ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጥቃት የምትከፍት ከሆነ በሞስኮ ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ለመጣል እየሰሩ መሆኑን ገልፀው ነበር።
የአሜሪካ የደህንነት ተቋማት “ሩሲያ እስከ 175 ሺህ ወታደሮቿን በማሰማራት ጎረቤቷ የሆነችው ዩክሬንን በቀጣይ ዓመት መለውረር እየተዘጋጀች ነው” ሲሉ ይደመጣል።
ክሬምሊን በበኩሏ “ማንንም የመውረር እቅድ የለኝም” በማለት የአሜሪካን ውንጀላ ያጣጣለች ሲሆን፤ ምእራባዊያን በሩሲያ ጠል አመለካከት (ሩሶፎቢያ) ታውረዋል ብላለች።
ሞስኮ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) መስፋፋት ሩሲያን እንደሚያሰጋ የተገለፀች ሲሆን፤ በአውሮፓውያኑ በ1991 ለሩሲያ የተሰጡ ዋስትናዎችን የሚጥስ ነውም ብላለች።