በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ከ130 በላይ ንጹሃን ሰዎች መገደላቸውን ኢሰመኮ ገለጸ
ኢሰመኮ በዚህ ሪፖርቱ ያካተታቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እጅግ አሳሳቢ የሆኑትን እና በምርመራ የደረሰባቸውን ብቻ መሆኑን ጠቅሷል
ኢሰመኮ "ከህግ ውጭ ግድያ፣ የሲቪል ሰዎች ሞት፣ዘረፋ፣ የጅምላ እና የታረዘሙ እስራቶች፣ አስገድዶ መድፈር፣ እገታ..." ተባብሰው ቀጥለዋል ብሏል
በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ከ130 በላይ ንጹሃን ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ) ዛሬ ባወጣው ሪፖርት ገለጸ።
ኢሰመኮ እንደገለጸው የትጥቅ ግጭት ባለባቸው በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች እንዳሁም ከግጭት አውድ ውጭ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተባብሰዋል።
መረጃዎችን እና ማስረጃዎችን ለመሰበሰብ የተለያዩ አካላትን ማነጋገሩን የገለጸው ኢሰመኮ "ከሕግ ውጭ ግድያ፣ የሲቪል ሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና ዘረፋ፣ የዘፈቀደ፣ የጅምላና የተራዘመ እስራትና የተፋጠነ ፍትሕ እጦት፣ አስገድዶ መሰወር፣ እገታ፣ እና የሀገር ውስጥ መፈናቀል" እጅግ አሳሳቢ ከሚባሉት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ውስጥ ቀዳሚዎቹ ናቸው ብሏል።
በዚህ ሪፖርት ያካተታቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እጅግ አሳሳቢ የሆኑትን እና በምርመራ የደረሰባቸውን ብቻ ነው መሆኑን የገለጸው ኢሰመኮ በተለያዩ ምክንያቶች የዘገዩ ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቅሷል።
ኢሰመኮ በአማራ ክልል ከየካቲት 15፣2016 እስከ ግንቦት 4፣2016 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ደግሞ ከታህሳስ 15፣2016 ዓ.ም እስከ ሚያዝያ 8፣2016ዓ.ም ተፈጽመዋል ያላቸውን የግድያ እና የዝርፊያ ወንጀሎችን ዘርዝሯል።
ኢሰመኮ እንደገለጸው በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በአማራ ክልል የተለያዩ ዞኖች በተፈጸሙ ጥቃቶች 28 ሰዎች ሲገደሉ በኦሮሚያ ክልል ደግሞ 103 ንጹሃን ሰዎች ተገድለዋል።
የተጠቀሱበት ድግግሞች ቢለያይም፣ በንጹሃን ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት በማድረስ የፌደራል መንግሰት የጸጥታ ኃይሎች፣ "ሸኔ" እና "የአማረ ታጣቂዎች" መሳተፋቸውን ገልጿል።
ኢሰመኮ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በሶማሌ፣ በሲዳማ፣ በአፋር እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች አስከፊ የሚባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ መሆናቸውን በዚህ ሪፖርቱ ጠቅሷል።
በአማራ ክልል እና ኦሮሚያ ክልሎች በንጹሀን ላይ የሰብአዊ ጥሰቶች የሚፈጸሙት፣ የፌደራል መንግስት የጸጥታ ሀይሎች ከታጠቁ ኃይሎች ጋር ከሚያደርጉት ግጭት ጋር በተያያዘ ነው ብሏል ኢሰመኮ።
በአማራ ክልል፣ የፌደራል መንግስት የጸጥታ ኃይል ከባለፈው አመት ሚያዝያ ጀምሮ ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ግጭት ውስጥ ገብቷል፤ ግጭቱ አሁንም አልቆመም።
በኦሮሚያ ክልል ደግሞ መንግስት 'ሸኔ' ብሎ በአሸባሪነት ከፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጋር የጀመረው የትጥቅ ግጭት አመታትን አስቶጥሯል።
በኦሮሚያ ክልል ላለው ግጭት መፍትሄ ይሰጣል ተብሎ የነበረው የፌደራል መንግስት እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ከወራት በፊት በታንዛኒያ ያደረጉት ድርድር ያለውጤት መጠናቀቁን መንግስት ማስታወቁ ይታወሳል።
መንግስት በአማራ ክልል የሚገኙ ታጣቂዎች ትጥቅ ፈትተው ወደ ሰላም እንዲመለሱ ጥሪ ከማድረግ ውጭ ለመደራደር ፍላጎት እንዳለው አልገለጸም።
የአሜሪካ መንግስት በቅርቡ ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ አጠቃላይ ተኩስ አቁም እንዲደረግ እና ከታጣቂዎቹ ጋር ንግግር እንዲጀመር ጥሪ አቅርቧል። ኢትዮጵያ ችግሯን እንዴት መፍታት እንዳለባት ለመምከር ሞክሯል ያለውን መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት በጽኑ መቃወሙ ይታወሳል።