ኢሰመኮ በአርባ ምንጭ ዙሪያ የተከሰተው ግጭት ከመባባሱ በፊት አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጠው አሳሰበ
በአስተዳደር መዋቅር ጥያቄ አቅራቢዎችና በጋሞ ዞን አስተዳደር መካከል በተፈጠሩ ግጭቶች የሰዎች ህይወት ማለፉንና ንብረት መውደሙንም ገልጿል
ከግጭቶቹ ጋር በተያያዘ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ ማቅረብ እንደሚገባም ኮሚሽኑ ጠይቋል
በጋሞ ዞን በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የተከሰተው ግጭት ከመባባሱ በፊት አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጠው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳስቧል።
ኢሰመኮ በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ፥ በአስተዳደር መዋቅር ጥያቄ አቅራቢዎች እና በጋሞ ዞን አስተዳደር መካከል ያለው ውጥረት እየተባባሰ መሄዱን አመላክቷል።
በአርባምንጭ ወረዳ ስር የሚገኙ ኤልጎ፣ ወዘቃ፣ ደምብሌ እና ጫሞ 01 የተባሉ አራት ቀበሌዎች ከጋሞ ዞን በመውጣት ልዩ ወረዳ ሆነው ለመደራጀት በተለያየ ጊዜ ጥያቄ ሲያነሱ መቆየታቸውን ያወሳው ኮሚሽኑ፥ ጥያቄው በተለይ ከ2010 ዓ.ም ጎልቶ መነሳት መጀመሩን ገልጿል።
ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የአስተዳደር መዋቅር ጥያቄ አቅራቢዎች በስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ፣ ለሁለቱም ምክር ቤቶች የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲን በመምረጣቸው ምክንያት የጋሞ ዞን አስተዳደር በተለያየ መንገድ ስልታዊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እየፈጸመብን ነው ብለው ያምናሉ።
የዞኑ አስተዳደር በበኩሉ የአስተዳደር መዋቅር ጥያቄ አቅራቢዎች በአካባቢ ምርጫው በማሸነፍ ስልጣን ሳይረከቡ መንግስት ቀበሌዎቹን ማስተዳደር የለበትም በሚል ምክንያት በአካባቢው የመንግሥት መዋቅር እንዲፈርስና አካባቢው እንዳይረጋጋ እያደረጉ ነው በሚል ወቀሳውን ያቀርባል።
በሁለቱ አካላት መካከል ያለው ውጥረት በተለይ ጥቅምት 11 2016 አንድ በወንጀል የተጠረጠረ ግለሰብ በኤልጎ ቀበሌ በፖሊስ በቁጥጥር ስር ውሎ በተፈጸመበት ድብደባ ከሞተ በኋላ ይበልጥ መባባሱን የኢሰመኮ መግለጫ ያመላክታል።
የጋሞ ዞን ፖሊስ ከግለሰቡ ግድያ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ ፖሊሶችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ምርመራ መጀመሩን ቢገልጽም በተለያዩ ሰዎችና ቡድኖች በተፈጸሙ ጥቃቶች በነዋሪዎች የሙዝ እርሻዎችና በመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ከፍተኛ የንብረት ውድመት ተከስቷል ነው ያለው ኮሚሽኑ።
ከኅዳር 16 2016 ጀምሮ በተለያዩ ጊዜዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት በግለሰቦች እና በጸጥታ አካላት በተወሰዱ የኃይል እርምጃዎች ለጊዜው ቁጥራቸው በትክክል ያልታወቀ ነዋሪዎች እና የጸጥታ አባላት ላይ የሞት እና የአካል ጉዳት መድረሱንም ጠቅሷል።
በግጭቱ ምክንያት በርካታ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ያለው ኢሰመኮ፥ የዘፈቀደ እስር እና እየተወሰዱ ያሉ የሀይል እርምጃዎች በነዋሪዎች ላይ ተጨማሪ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዳያስከትሉ ስጋት አለኝ ብሏል።
የፌዴራል እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ከአካባቢው ነዋሪዎች እና ከዞኑ አስተዳደር ጋር በመነጋገር በአፋጣኝ ውጥረቱን እንዲያረግቡም ነው ኢሰመኮ ጥሪ ያቀረበው።
ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች በቂ የሆነ አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲቀርብና ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመልሰው በዘላቂነት የሚቋቋሙበት ሁኔታ እንዲመቻችም ጠይቋል።
የአስተዳደር መዋቅር ጥያቄ አቅራቢዎችም በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ጥያቄያቸውን በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ ብቻ ማቅረብ አለባቸው ብሏል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በመግለጫው።