በአለም አቀፍ ደረጃ ከ733 ሚሊየን በላይ ሰዎች በርሀብ ውስጥ እንደሚገኙ ተነገረ
ከዚህ ውስጥ አብዘሀኛዎቹ በአፍሪካ እና እስያ ውስጥ የሚገኙ ናቸው ተብሏል
የአለም ንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የአለም አቀፍ ንግድ ስርአት መዛባት በድህነት ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ኑሮ እጅግ እየጎዳ ነው ብለዋል
በአለም አቀፍ ደረጃ ከ733 ሚሊየን በላይ ሰዎች በርሀብ ውስጥ እንደሚኖሩ ተነግሯል፡፡
የአለም ንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ንጎዚ ኦኮንጆ ኢዋላ የምግብ ዋስትና መሸርሸር እና አለም አቀፍ የንግድ ስርአት መዛባት በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች የሚኖሩባቸውን ሀገራት ከአቅማቸው በላይ እየፈተነ ነው ብለዋል፡፡
በጣሊያን ሮም በተካሄደው የምግብ ፎረም ላይ ንግግር ያደረጉት ዳይሬክተሯ ፤ አሁን ባለንበት ፍጥነት በ2030 ረሃብን እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን በማስወገድ ዘላቂ የልማት ግብን አናሳካም ነው ያሉት።
55 በመቶው አለም አቀፍ የምግብ ምርት የሚመረተው የውሀ እጥረት በሚገኝባቸው አካባቢዎች እንደሆነ በመድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥ የምግብ ዋስትናን አደጋ እየጣለ እንደሚገኝ የተናገሩት ዳይሬክተሯ ፤በውሃና በመሬት አያያዝ፣ በብዝሀ ህይወት መመናመን እና የደን መጨፍጨፍ በሁሉም የምግብ ስርዓታችን ላይ ተጽእኖ በማሳደር የዘርፉን ችግሮች እያባባሰ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በመድረኩ ላይ የግብርና ምርት እና ፍጆታ በንግድ ገደቦች እንዲሁም ድጎማዎች የተዛባ ሆኖ መቀጠሉ ተመላክቷል፡፡
በኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት (OECD) የተተነተነው መረጃ እንደሚያመላክተው ከ2020 እስከ 2022 በአማካይ 630 ቢሊዮን ዶላር በ54 ሀገሮች ለግለሰብ አምራቾች ድጋፍ መሰጠቱ ፍትሀዊ የንግድ ውድድርን እንደጎዳ ተነግሯል፡፡
ከዚህ ባለፈም ይህ ድጋፍ ብዙውን ጊዜ የአካባቢን ጉዳትን እንደሚያስከትል ፣ መሬት ከአቅም በላይ እንዲታተረስ እና የምርት መጠኑ እንዲቀንስ እንዲሁም ውሃን ከመጠን በላይ መጠቀምን ያበረታታል ነው የተባለው፡፡
የአለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) እንዳለው አሁን ያለው የግብርና እና ምግብ ስርዓታችን የሚያስከትለው አካባቢያዊ እና የጤና ጉዳት በዓመት 10 ትሪሊዮን ዶላር የሚገመት ኪሳራ የሚያደርስ ነው፡፡
የግብርና እና የምግብ ዋስትና ችግሮችን ለመቅረፍ የንግድ ስርአት እና የዓለም ንግድ ድርጅት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ንጎዚ ኦኮንጆ ኢዋላ ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም ነጻ፣ ፍትሃዊ፣ ክፍት እና ሊተነበይ የሚችል የባለብዙ ወገን የግብይት ስርዓት እንዲሁም የዘመኑ የንግድ ሂደቶች ዛሬ እና ወደፊት ለአለም ህዝብ አስተማማኝ የምግብ ዋስትና ለመፍጠር የሚያስችል የግብርና ስርዓት ለመገንባት ወሳኝ ናቸው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በግብርና ምርምሮች ፣ ምርጥ ዘሮች ፣ አስቸጋሪ የአየር ንብረትን መቋቋም የሚችሉ የግብርና ስርአቶች ፣ አረም እና ነፍሳትን መቆጣጠር የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ላይ የምግብ እና እርሻ ድርጅት እና የአለም ንግድ ድርጅት በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል፡፡