የእጩዎች የምዝገባ ቀን እስከተያዘው ወር መጨረሻ ተራዘመ
እጩዎች እና የግል ተወዳዳሪዎች ከየካቲት 8 እስከ 21 እንዲመዘገቡ የጊዜ ሰሌዳው መውጣቱ የሚታወስ ነው
አዲስ አበባ እና ድሬዳዋን ጨምሮ በ4 የተለያዩ ክልሎች ሲካሄድ የነበረው የእጩዎች ምዝገባ መጠናቀቁን ቦርዱ አስታውቋል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋን ጨምሮ በ4 የተለያዩ ክልሎች ሲካሄድ የነበረው የእጩዎች ምዝገባ መጠናቀቁን አስታወቀ፡፡
ምዝገባውን በማስመልከት ሶስት የተለያዩ ምክክሮችን ከፓርቲዎች ጋር አድርጊያለሁ ያለው ቦርዱ ምዝገባው ቀድሞ በተጀመረባቸው የከተማ መስተዳድሮች እና ክልሎች ማለትም በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ እንዲሁም በኦሮሚያ፣ በሃረሪ፣ በጋምቤላ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ትናንትና ሃሙስ የካቲት 25 ቀን 2013 ዓ/ም መጠናቀቁን አስታውቋል፡፡
ምዝገባው ዘግይቶ በተጀመረባቸው የአማራ፣ የሶማሌ፣ የአፋር፣ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና የሲዳማ ክልሎች እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ምእራብ እና ምስራቅ ወለጋ ዞን አካባቢዎች ዛሬ የካቲት 26 ቀን 2013 ዓ.ም ነበር ሊጠናቀቅ የሚገባው ቦርዱ በያዘው በመርሃ ግብር መሰረት፡፡
ሆኖም በቢሮዎች መከፈት መዘግየት እንዲሁም በትራንስፓርትና በሌሎችም ተያያዥ ችግሮች የተነሳ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
ያጋጠሙትን ችገሮች እና የፓርቲዎችን አቤቱታዎች ከግምት ውስጥ አስገብቻለሁ ያለው ቦርዱም ሁለተኛው ዙር የእጩዎች ምዝገባ እስከ የካቲት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ መራዘሙን አስታውቋል፡፡
ፓርቲዎች በተሰጡት ተጨማሪ ቀናት ውስጥ ምዝገባውን አንዲያጠናቅቁም አሳስቧል፡፡
ቦርዱ ከአሁን ቀደም የፓርቲ እጩዎች እና የግል ተወዳዳሪዎች ከየካቲት 8 እስከ 21 እንዲመዘገቡ ሲል በምርጫ የጊዜ ሰሌዳው ማስቀመጡ የሚታወስ ነው፡፡