ኦነግ ባደረገው የፍርድ ቤት ክርክር ምርጫ ቦርድ ያሳለፈው ውሳኔ ቢሻርም ቦርዱ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠይቋል
የ6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ድምጽ መስጫ ቀን የፊታችን ሰኔ 14 ሰኞ እለት እንደሆን ቦርዱ ወስኗል።
ኦነግ በውስጥ ችግሩ ምክንያት ጠቅላላ ጉባዔ ሳያካሂድ በመቆየቱ “የምርጫና የዕጩ ምዝገባ ጊዜ አልፎብናል” በማለት ቦርዱ ችግሩን ግምት ውስጥ በማስገባት የምልክት መረጣና የዕጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ እንዲያደርግ እንዲፈቅድለትና ጠቅላላ ጉባኤውንም እንዲያጸድቅለት ቦርዱን በደብዳቤ ጠይቆ ነበር።
ቦርዱም የቀረቡትን ሰነዶች በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 እና በፓርቲው ህገ ደንብ መሰረት መርምሮ ባሳለፈው ውሳኔ፤ አዲስ የተመረጡትን የኦነግ አመራሮች እና የተካሔደውን ጉባኤ እንደማይቀበል አስታውቋል፡፡
በዚህ መሰረት ኦነግ የቦርዱን ውሳኔ ተቃውሞ ወደ ፈረድ ቤት ወስዶ ሲከራከር ቆይቶ ፍርድ ቤትም የቦርዱን ውሳኔ ውድቅ አድርጓል።
የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነ አራርሶ ቢቂላ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም ያደረገውን የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ እና በስብሰባው ያሳለፈውን ውሳኔ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲቀበለው ወስኖ ነበር።
የቦርዱ ኮሙንኬሽን ሀላፊ ወይዘሪት ሶልያና ሽመልስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ላይ የኦነግን የፍርድ ቤት ውሳኔ እንዴት ልታስኬዱት ነው ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።
ኦነግ በምርጫው መወዳደር የሚያስችለውን የምርጫ ስራዎች የጊዜ ሰለዳዎች ስላለፉት በዘንድሮው ምርጫ ላይ መወዳደር እንደማይችል ወይዘሪት ሶልያና ተናግረዋል።
ኦነግ በፍርድ ቤት ተወስኖልኛል እና በምርጫው ልሳተፍ ብሎ ቦርዱን እንደጠየቀ ወ/ሪት ሶልያና ተናግረዋል።
ይሁንና ፓርቲው ለምርጫ ፉክክር የሚያበቁ ስራዎች ስላለፉት ፓርቲው በምርጫው ለመሳተፍ የሚያበቃ ጊዜ ስለሌለው እንዳይሳተፍ ቦርዱ መወሰኑን ተናግረዋል።
ለአብነትም ፓርቲው የመራጮች ምዝገባ፤ የእጩ ተፎካካሪዎች ምዝገባ እና ሌሎች በምርጫው እንዲሳተፍ የሚያበቁ ስራዎችን አልፈውታል ብለዋል።
የኦነግ የፍርድ ቤት ውሳኔ ላይ ቦርድ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠይቆ ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውንም ወ/ሪት ሶልያና ተናግረዋል።
ይህ በዚህ እንዳለ 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲካሄድ የወሰነ ሲሆን የመራጮች ምዝገባ ቅሬታ በቀረበባቸው ምርጫ ጣቢያዎች እና በተለያዩ ምክንያቶች ተፈናቃይ ዜጎች ያሉባቸው አካባቢዎች ምርጫው ከሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በኋላ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
አጠቃላይ የምርጫ ውጤት ደግሞ ምርጫ እንደሚካሄድባቸው አስቀድመው በቦርዱ በተለዩ ክልሎች እና ከተማ አስተዳድሮች ላይ ምርጫው ከተካሄደ በኋላ ለህዝብ ይፋ እንደሚሆንም ቦርዱ ገልጿል።
ከሰኔ 14 በኋላ ምርጫ የሚካሄድባቸው ቦታዎች መካከል በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኘው መተከል እና ሌሎች ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው ቦታዎች አይካሄድም።
የመራጮች ድምጽ መስጫ ወረቀት በUNDP የገንዘብ እርዳታ በውጭ አገራት ታትሞ እስከ ግንቦት መጨረሻ ወደ አገር ውስጥ እንደሚገባም ተገልጿል።