“በተያዘለት ቀን አይካሄድም፤ በአንድ ቀን ግን ይካሄዳል” የተባለለት 6ኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ
ፓርቲዎች ከተራዘመ አይቀር ግብርናውን በማያስተጓጉልና እየተነሱ ላሉ ጥያቄዎች ምላሽ ሊሰጥ በሚችል መንገድ እንዲካሄድ ጠይቀዋል
ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ/ም እንደማይካሄድ የተነገረለት ምርጫው በሳምንታት ሊራዘም እንደሚችል ተጠቁሟል
የዘንድሮው ምርጫ አሁን ላይ እየታዩ ላሉ የዲሞክራሲ ጥያቄዎች ምላሽ በሚሰጥ መንገድ እንዲራዘም ተጠየቀ።
የምርጫ ድምጽ መስጫው ቀን የግብርና ስራውን በማያስተጓጉል መንገድ እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዋች ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ዙሪያ በአዲስ አበባ መክሯል።
በመድረኩ ላይ ትላንት የተጠናቀቀውን የመራጮች ምዝገባ በተመለከተ እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል።
እስከ ግንቦት 4 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስም 36 ሚሊዮን 245 ሺህ 444 ሰዎች የምርጫ ካርድ ወስደዋል ተብሏል።
ምርጫ ካርድ ከወሰዱት ውስጥ 16.6 ሚሊዮኑ ሴት ፤ 19.5 ሚሊዮኑ ወንድ ናቸው፡፡
50 ሚሊዬን ዜጎች ካርድ ሊወስዱ እንደሚችሉ ተገምቶ ነበር፡፡ አሁን ያለው ካርድ የወሰዱ ዜጎች ቁጥሩ የግምቱን 78 በመቶ ሸፍኗል።
ጋምቤላ፣ አዲስ አበባ፣ ሶማሌ እና አፋር ክልሎች ከተገመተው በላይ የመራጮች ካርድ የተወሰደባቸው ናቸው።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአንጻራዊነት ዝቅተኛ የመራጮች ምዝገባ የተከናወነበት ክልል መሆኑን ቦርዱ አስታውቋል።
ቦርዱ አክሎም ምርጫው በተያዘለት ቀን እንደማይካሄድ አስታውቋል።
ከአሁን ቀደም በሁለት የተለያዩ ቀናት እንደሚካሄዱ ተገልጸው የነበሩት የአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ምርጫዎች ከሃገር አቀፉ ምርጫ ጋር በአንድ ቀን እንዲካሄዱም ቦርዱ ወስኗል፡፡
ቦርዱ ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም ለማካሄድ የያዘውን እቅድ የመራጮች ምዝገባ እና ሌሎችም ስራዎች በተያዘላቸው ቀን ባለመጠናቀቃቸው ምክንያት ድምጽ መስጫው ቀን በ3 ሳምንታት እንዲራዘም ቦርዱ ፓርቲዎቹን ጠይቋል፡፡
ቦርዱ በምርጫ ድምጽ መስጫ ቀኑ ላይ ያለውን ለፓርቲዎች ለውይይት ከከፈተ በኋላ ፓርቲዎቹ አቋማቸውን ለቦርዱ አስታውቀዋል።
የእናት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ሠይፈስላሴ አያሌው (ዶ/ር) ምርጫው ሊራዘም እንደሚችል ይጠብቁ እንደነበር ገልጸው የመራጮች ድምጽ መስጫ ቀኑ ሲራዘም የግብርና ስራውን በማይጎዳ መንገድ ይሁን ብለዋል።
የኦሮሚያ ነጻነት ንቅናቄ (ኦነን) ፓርቲ በበኩሉ የተራዘመው የመራጮች ድምጽ መስጫ ቀኑ ከመጭው ክረምት በኋላ እንዲሆን ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ህብረት ሊቀመንበር አቶ ገብሩ በርሄ ደግሞ ምርጫው ከተራዘመ አይቀር አሁን እየተነሱ ያሉ የዲሞክራሲ እና የተሳትፎ ጥያቄዎችን በሚመልስ መልኩ ቢራዘም የተሻለ እንዲሆን ለምርጫ ቦርድ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።
የአፋር ህዝብ ፓርቲ ደግሞ የምርጫ ድምጽ መስጫ ቀን ከተራዘመ የመራጮች ምዝገባ ቀንም ሊራዘም እንደሚገባ ጠይቋል።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ በበኩላቸው ፓርቲዎቹ ያነሷቸው ጥያቄዎች ለቦርዱ ቀጣይ ውሳኔዎች ግብዓት መሆናቸውን በመጠቆም የድምጽ መስጫ ቀኑን የተነሱ ሀሳቦችን ከግምት ውስጥ በማስገባት በቀጣይ ውሳኔ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
ለመራጮች ምዝገባ በቂ ጊዜ መሰጠቱን የተናገሩት ሰብሳቢዋ የምዝገባ ጊዜው በድጋሚ ሊራዘም እንደማይችል ገልጸው ፓርቲዎች ተጨማሪ ጥያቄዎች እና የውሳኔ ሀሳቦች ካሏቸው በጽሁፍ ለቦርዱ ለማስገባት እንደሚችሉ አስታውቀዋል።