ቀጣዩ ምርጫ ኢትዮጵያን ለተጨማሪ ቀውስ እንዳይዳርጋት ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ የሕግ ባለሙያዎች ገለፁ
6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሦስት ሳምንታት እንዲራዘም ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ሀሳብ ማቅረቡ ይታወቃል
ውብሸት ሙላት የተባሉ የሕግ ባለሙያ “ምርጫው የባሰ ሀገርን ማፍረሻ ምክንያት እንዳይሆን እሰጋለሁ “ ብለዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ ርዕሰ መስተዳድር ከሆኑ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው ምርጫ ለተጨማሪ ጊዜ እንዲራዘም ተወስኗል፡፡
በመደበኛው መንገድ 2012 ዓ.ም ይካሄድ የነበረው ይህ ምርጫ ፣ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ በ2013 ዓ.ም ግንቦት 28 ሊሚካሄድ ቀን ተቆርጦለት የነበረ ቢሆንም ቦርዱ በ3 ሳምንታት እንዲራዘም ሀሳብ አቅርቧል፡፡ ትክክለኛው የጊዜ መጠን ግን ወደ ፊት የሚታወቅ ነው፡፡
አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ያለው ግድያና መፈናቀል እንዲሁም ጦርነት ምርጫውን ሊያደናቅፈው እንደሚችል በመገመት ምርጫው ይተላለፍ እያሉ ናቸው፡፡ በወለጋ፣ በመተከል፣ በአጣዬ፣ በቀወት፣ በአፋር እና ሱማሌ ክልሎች፣ በአማሮ ኬሌ እና በሌሎችም ቦታዎች ያሉት ሰብዓዊ ቀውሶችና በትግራይ ክልል ያለው ጦርነት እልባት ሳያገኝ ምርጫ መደረግ የለበትም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡
በሌላ ወገን ያሉት ደግሞ ኢትዮጵያ በችግር ውስጥ ያለችም ቢሆን ምርጫው መደረግ አለበት የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ የደህንነት አማካሪ ሚኒስትርና የምርጫ ጉዳይ ደህንነትና ጸጥታ ኮሚቴ ሰብሳቢ ገዱ አንዳርጋቸው ፣ የአሁኑ የኢትዮጵያ ምርጫ በሽግግር ሂደት ውስጥ የሚካሄድ ምርጫ በመሆኑ አንዳንድ የጸጥታ እንቅፋቶች ሊያገጥሙ እንደሚችሉ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ የመንግስት አጠቃላይ ግምገማ ከሀገሪቱ ስፋትና የምርጫ ሰፊ ዝግጅት አንጻር የጸጥታ ችግር የሚያጋጥማቸው አካባቢዎች ተጽዕኖ የከፋ እንደማይሆን እንደሚያመለክትም አቶ ገዱ ገልጸዋል፡፡
የሕግ ባለሙያው አቶ ውብሸት ሙላት ለአል ዐይን አማርኛ በሰጡት አስተያየት ፣ ከትግራይ ክልል በተጨማሪ “ምርጫ የማይደረግባቸው ሌሎችም አካባቢዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ” ገልጸው ፣ ይህ ሁኔታ ሀገሪቱ በጸጥታ ረገድ ምን ደረጃ ላይ እንዳለች በራሱ ምስክር እንደሆነ ያነሳሉ፡፡ አሁን ላይ ያለው የጸጥታ ችግር እስከ ምርጫው ቀን ድረስ ሊባባስ ወይም ሊሻሻል እንደሚችል ያነሱት አቶ ውብሸት ፣ በምርጫው ላይ በትክክል ሊፎካከሩ የሚችሉ ፓርቲዎች መኖር አለመኖራቸውን በሚመለከትም አስቸጋሪ ሁኔታ እንዳለ ግልጽ ነው ይላሉ፡፡
ስለ ኦሮሚያ ክልል በተለየ ሁኔታ ያነሱት አቶ ውብሸት “በኦሮሚያ ክልል ከተወሰኑ የምርጫ ወረዳዎች በስተቀር” ተፎካካሪ ፓርቲ አለመኖሩን እና ከገዥው ኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ በስተቀር ውድድር እየተደረገ ነው ማለት አስቸጋሪ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አቶ ውብሸት ሙላት፣ ከሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች አንጻር ኦሮሚያ ክልል ምርጫ ለመወዳደር ምቹ እንዳልሆነ ነው የሚገልጹት፡፡
በአጠቃላይ አሁን ኢትዮጵያ ካለችበት ሁኔታ አንጻር ሲታይ ፣ ምርጫው “የባሰ ሀገርን ማፍረሻ ምክንያት (መንስኤ) እንዳይሆን እሰጋለሁ” ብለዋል የሕግ ባለሙያው፡፡ ምርጫ ከመካሔዱ አስቀድሞ ካሉት ምልክቶችና ስጋቶች አንጻር ከመዘንነው “የምርጫውን ውጤት ተከትሎ ሌላ የጸጥታ ችግር አይኖርም ማለት ያስቸግራል” ይላሉ። ከዚህ ባለፈም ከፍተኛ የጸጥታ ችግር ቢፈጠር ያንን መቆጣጠር የሚያስችል አቅም አለን ወይ? የሚለው ጉዳይም ትልቅ ነጥብ እንደሆነ የሕግ ባሙያው አቶ ውብሸት ያነሳሉ፡፡
ሌላው የሕግ ባለሙያና ጠበቃ አቶ ሞላልኝ መለሰ ፣ መጪው ምርጫ ለሀገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው እና ምናልባትም የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደቱን ወደፊት የማስፈንጠር አቅም ያለው ቢሆንም በፀጥታ እና በደህንነት ስጋት ውስጥ የሚከናወን መሆኑ ምርጫው በራሱ ሌላ ችግር እንዳይሆን ስጋትን እንደሚፈጥር አንስተዋል፡፡
መንግስት ለመራጮችም ሆነ ለእጩ ተወዳዳሪዎች እምነትን የሚፈጥር ሰላማዊ ፣ ሕግ እና ስርዓት የተከበረበት ከባቢያዊ ሁኔታን ካልፈጠረ ፣ ምርጫው ሀገሪቱን ወደ ባሰ ችግር እንደሚያስገባም አቶ ሞላልኝ ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡
አቶ ሞላልኝ መንግስት ሰላም እና ደሕንነት የማስከበር ተግባሩን በሚገባ ተወጥቶ ምርጫው ሰላማዊ እና ሕጋዊ ሁኔታዎች በተከበሩበት መንገድ ከተከናወነ ፣ በሀገሪቱ ታሪክ ላይ አዎንታዊ አሻራውን ትቶ እንደሚያልፍ ነው ሀሳባቸውን የሰጡት፡፡
በመሆኑም ምርጫው ሀገሪቱን ለባሰ ችግር እንዳይዳርጋት ሁሉም አካላት ሊያስቡበት እና ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የሕግ ባለሙያዎቹ ገልጸዋል፡፡
በስጋትና በተስፋ ለሚጠበቀው ለቀጣዩ ምርጫ በመላው ሀገሪቱ ድምጽ የሚሰጡባቸው ከ50 ሺህ በላይ የምርጫ ጣቢያዎች የተዘጋጁ ሲሆን የመራጮች ምዝገባን ከ152 ሺህ በሚበልጡ ባለሙያዎች ሲከናወን ቆይቷል፡፡