የሱዳንን ቀውስ ለመፍታት የተጀመረው ድርድር “ግማሽ መንገድ ላይ ቆሟል”ተባለ
ድርድሩ የቆመው ወታደራዊ አመራሩ ወደ ቀደመ ሁኔታው ለመመስ ፍቃደኛ ባለመሆኑ ነው ተብሏል
የሱዳን ወታደራዊ አመራር ጠቅላይ ሚኒስትር አብዳላ ሀምዶክ ማሰሩን ተከትሎ ሀገሪቱ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ገብታለች
ከስልጣን ለተወገዱት ለሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ቅርብ የሆኑ ሁለት ምንጮችን ጨቅሶ እንደዘገበው፤ቀውሱን ለፍታት የተጀመረው ድርድር ቆሟል፡፡
የድርድር ሂደቱ ሊቆም የቻለው የሱዳን ወታደራዊ ክንፉ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር መንገድ ለመመለስ ፍቃደኛ ባለመሆኑ እንደሆነ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የሱዳን ሉአላዊ የሽግግር ምክርቤት ፕሬዝዳንት የሆኑት ጄነራል አልቡርሃን፣ጠቅላይ ሚኒስትር አብዳላ ሀምዶክንና ሌሎች የሲቪል አስተዳደሩ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ማሰራቸውን ተከትሎ ሀገሪቱ ፖለቲካዊ ቀውስ ገብታለች፡፡
- ሃምዶክ ይመሰረታል የተባለውን የሱዳን አዲስ መንግስት ለመምራት ተስማምተዋል ተባለ
- መፈንቅለ መንግስት አድራጊው የሱዳን ጄነራል 4 ሚኒስትሮችን ከእስር ለመልቀቅ መወሰናቸውን አስታወቁ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክና የሲቪል መንግስቱ ባለስልጣናትን ከስልጣን ያነሱት የሱዳን ጦር አዛዥ አል ቡርሃን በሀገሪቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጃቸው ይታወሳል፡፡
ከዚህ ባለፈም፤ አል ቡርሃን በአሜሪካ፣ በአውሮፓ ህብረት እና በፈረንሳይ የሚገኙትን ጨምሮ በሌሎች ሀገራት የሚገኙ የሱዳን አምባሳደሮችን ከስራ ማባረራቸው አይዘነጋም፡፡
ዲፕሎማቶቹ የሱዳን የሽግግር መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አብደላ ሃምዶክን በመደገፋቸው ከኃላፊነት መነሳታቸው መገለጹ የሚታወስ ነው፡፡
አልቡርሃን ይህን እርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት በሱዳን የጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዲክንና ወታረደራዊ አመራሩን የሚደግፉና የሚቃወሙ ሰልፎች ተካሂደው ነበር፡፡
ወታደራዊ አመራሩ አሁን በቁም እስር ላይ የነበሩትንና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናትን ከእስር የለቀቁ ሲሆን ያለው ሁኔታ ከወታደራዊ እርምጃው በፊት ወደ ነበረው ሁኔታ እንዲስተካከል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፈልጋሉ፡፡ ነገርግን በወታደራዊ አመራሩ በኩል ከውጭ ያለውን ጫና ከግምት በማስገባት ለመደራደር ቢፈግጉም ድርድሩ እስካሁን ወደ መፍትሄ ማምጣት አልቻለም፡፡