ፖለቲካ
ሃምዶክ ይመሰረታል የተባለውን የሱዳን አዲስ መንግስት ለመምራት ተስማምተዋል ተባለ
የጦሩ እና የሲቪል ባለስልጣናቱን ለማሸማገል ጥረቶች በመደረግ ላይ ናቸው
ሆኖም ሃምዶክ ወደመሪነት ከመመለሳቸው በፊት ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጠዋል ተብሏል
በሱዳን ጦር በተመራው መፈንቅለ መንግስት ከጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው የተወገዱት አብደላ ሃምዶክ አዲስ የሚመሰረተውን መንግስት ለመምራት መስማማታቸው ተነገረ፡፡
ዘ ናሽናል ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች የሃምዶክን መስማማት ገልጸውልኛል ብሏል፡፡
ሆኖም የአብደላ ሃምዶክ ወደ መንግስት መሪነት መመለስ ራሳቸው አስቀምጠዋቸዋል በተባሉ የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
ቅድመ ሁኔታዎቹም ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ይለቀቁና በሽግግር ጊዜ ህገ መንግስቱ ላይ የተጣለው እገዳ ይነሳ የሚሉ ናቸው፡፡
በሌ/ጄ አብዱልፈታህ አል ቡርሃን በተመራውና ሃምዶክን አሁንም ጭምር ለቁም እስረኝነት በዳረገው መፈንቅለ መንግስት የሃገሪቱን የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ካሊድ ዑመር የሱፍን ጨምሮ ሌሎች ባለስልጣናት መታሰራቸው የሚታወስ ነው፡፡
ይህን ተከትሎ በጦሩ እና በሲቪል ባለስልጣናቱ መካከል ያለውን ልዩነት ለማረቅ የሚያስችሉ የማሸማገል ጥረቶች በመደረግ ላይ ናቸው፡፡