የቀድሞው የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከእስር ከተለቀቁ አንድ ቀን በኋላ ታሰሩ
ኢብራሂም ዳንጉር የታሰሩት ከአንድ ዓመት በፊት በፖለቲካ ሴራ ተጠርጥረው ነበር
ኢብራሂም ዳንጉር በፕሬዝዳንት አልበሽር የስልጣን ዘመን ከፓርቲ ኃላፊነት እስከ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት አገልግለዋል
የቀድሞው የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢብራሂም ዳንጉር ከእስር ከተለቀቁ አንድ ቀን በኋላ በድጋሚ መታሰራቸው ተነግሯል።
በቀድሞው የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር የስልጣን ዘመን ከፓርቲ ሀላፊነት እስከ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት በመሆን ያገለገሉት ኢብራሂም ዳንጉር ትናንት ምሽት ከእስር ተፈተው ነበር።
ኢብራሂም ዳንጉር ትናንት ምሽት ከእስር ተፈትተው ቤተሰባቸውን እንደተቀላቀሉ ከቤተሰቡ መስማቱን በካርቱም የሚገኘው የአልአይን ዘጋቢ ተናግሯል።
የቀድሞው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለእስር የተዳረጉት ከአንድ ዓመት በፊት በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን የተነሱት ፕሬዝዳንት አልበሽርን ወደ ስልጣን ለመመለስ የፖለቲካ ሴራ ውስጥ ተሳትፈዋል በሚል ተጠርጥረው እንደሆነ ዘገባው አክሏል።
ኢብራሂም ዳንጉር ከእስር እንዲለቀቁ የሱዳን ጸረ ሽብር መርማሪ ፍርድ ቤትን ጠይቆ የነበረ ቢሆንም፤ ግለሰቡ ለመፈንቅለ መንግስት እየተዘጋጁ ነው በሚል ጥያቄው ውድቅ ተደርጎ ነበርም ተብሏል።
ይሁንና ግለሰቡን ጨምሮ ሰባት ሰዎች ዛሬ ረፋድ በድጋሜ በሱዳን ጦር ለእስር መዳረጋቸውም ተነግሯል።
ከአንድ ሳምንት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክና የሲቪል መንግስቱ ባለስልጣናትን ከስልጣን ያነሱት የሱዳን ጦር አዛዥ አል ቡርሃን በሀገሪቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጃቸው ይታወሳል።
ከዚህ ባለፈም፤ አል ቡርሃን በአሜሪካ፣ በአውሮፓ ህብረት እና በፈረንሳይ የሚገኙትን ጨምሮ በሌሎች ሀገራት የሚገኙ የሱዳን አምባሳደሮችን ከስራ ማባረራቸው አይዘነጋም።
ዲፕሎማቶቹ የሱዳን የሽግግር መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አብደላ ሃምዶክን በመደገፋቸው ከኃላፊነት መነሳታቸው መገለጹ የሚታወስ ነው።