መፈንቅለ መንግስት አድራጊው የሱዳን ጄነራል 4 ሚኒስትሮችን ከእስር ለመልቀቅ መወሰናቸውን አስታወቁ
ይፈታሉ ከተባሉት ሚኒስትሮች መካከል የኮሙኒኬሽን፣ የባህል እና የስፖርት ሚኒስትሮች ይገኙበታል
ሚኒስትሮቹ ቡርሃን ከመሩት መፈንቅለ መንግስት ጋር በተያያዘ ነበር በጦሩ የታሰሩት
መፈንቅለ መንግስት አድራጊው የሱዳን ጦር መሪ ሌ/ጄ አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን አራት ሚኒስትሮችን ከእስር ለመልቀቅ መወሰናቸውን አስታወቁ፡፡
ሚኒስትሮቹ ከ10 ቀናት በፊት ቡርሃን ከመሩት መፈንቅለ መንግስት ጋር በተያያዘ ነበር በጦሩ የታሰሩት፡፡
ነገር ግን አሁን ሚኒስትሮቹ እንዲፈቱ መወሰኑን የሃገሪቱ ጦር ጠቅላይ አዛዥ ሌ/ጄ አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን አስታውቀዋል፡፡
ከእስር ይፈታሉ የተባሉት ሚኒስትሮች የኮሙኒኬሽን ሚኒስትሩ ሃሺም ሃሰብ አል ረሱል፣ የባህል እና መረጃ ሚኒስትሩ ሃምዛ ባሉል፣ የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስትሩ ዩሱፍ አደም አል ዲ እና የንግድ እና አቅርቦት ሚኒስትሩ አሊ ጌዶ ናቸው፡፡
ሰኞ ጥቅምት 14 ቀን 2014 ዓ/ም በተካሄደው መፈንቅለ መንግስት ጦሩ በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ይመራ የነበረውን የሲቪል መንግስት አስወግዷል፡፡
የሃገሩቱን ህገ መንግስት ጨምሮ ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤቱንና ሌሎችንም ሲቪል አደረጃጀቶች አፍርሷል፡፡
ሆኖም ጦሩ የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ ከፍተኛ ውግዘት እና መገለል ደርሶበታል፡፡ የሲቪል መንግስቱን ወደነበረበት እንዲመልስ የሚደረጉ ዓለም አቀፍ ጫናዎች መበርታታቸውን ተከትሎ አብደላ ሃምዶክን ጨምሮ እነዚህን ሚኒስትሮች ከእስር ፈቷል፡፡
ቡርሃን ከሰሞኑ በተማሩ (ቴክኖክራትስ) የሚመራ መንግስት እንደሚመሰረት ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው፡፡