ግለሰቡ በሚኖርበት መኖሪያ ቤት ውስጥ ተገድሎ መገኘቱ ተገልጿል
በስዊድን እና ዴንማርክ ቁርዓንን በማቃጠል የሚታወቀው ሰው ተገድሎ ተገኘ፡፡
ሳልዋን ሞሚካ በመባል የሚታወቀው ኢራቃዊ በፈረንጆቹ 2021 ላይ በስዊድን እና ዴንማርክ በእስልማና ሀይማኖት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ቁርዓንን ሲያቃጥል ታይቷል፡፡
ይህን ተከትሎም በበርካታ ሀገራት ተቃውሞ የተነሳበት የነበረ ሲሆን ጥገኝነት በሰጡት ሀገራት ላይ ቁጣ ተነስቶባቸው ነበር፡፡
ስዊድን እና ዴንማርክ ቁርዓንን ማቃጠል በህግ የሚከለክል ህግ የሌላቸው በመሆኑ በህግ ተጠያቂ ለማድረግ እንደሚቸገሩ በወቅቱ ቢናገሩም በተለያዩ ሀገራት ያሉ ኢምባሲዎቻቸው ከጥቃት አልዳኑም፡፡
ይህ በዚህ እንዳለም ሞሚካ በሚኖርበት በስዊድን መዲና ስቶኮልም መኖሪያ ቤት ውስጥ ተገድሎ እንደተገኘ አናዳሉ የሀገሪቱ መንግስታዊ ብዙሃን መገናኛን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡
የ38 ዓመቱ ሳልዋን ሞሚካ ትናንት ምሽት ሳይገደል አልቀረም የተባለ ሲሆን ፖሊስ የገዳዩን ማንነት ለመለየት ምርመራ እያደረገ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
ስዊድን በቅርቡ ቁርዓንን ማቃጠል የሚያስቀጣ ወንጀል መሆኑን የሚደነግግ ህግ ማዘጋጀቷ ይታወሳል፡፡
ግለሰቡ በስዊድን ደህንነት እየተሰማኝ አይደለም በሚል ወደ ኖርዌይ የተሰደደ ቢሆንም ህጋዊ ሰነድ የለውም በሚል ወደ ስዊድን መልሳዋለች፡፡
የስቶኮልም ፖሊስ እንደገለጸው ከሆነ የሞሚካ ግድያ በማህበራዊ ትስስር ገጾች በቀጥታ ሊተላለፍ ስለሚችል ምርመራ አደርጋለሁም ብሏል፡፡