ሶስተኛው ዙር የታጋቾችና እስረኞች ልውውጥ ከእስራኤል የሚለቀቁ ፍልስጤማውያን እስረኞችን ቁጥር 400 ያደርሰዋል
የፍልስጤሙ ሃማስ በዛሬው እለት ሶስት እስራኤላውያን ታጋቾችን እንደሚለቅ ተገለጸ።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ ዛሬ የሚለቀቁት ታጋቾች አርቤል የሁድ፣ አጋም በርገር እና ጋዲ ሞሰስ ናቸው ብሏል።
ሃማስ የ20 አመቷን የእስራኤል ወታደር አጋም በርገር ለአለማቀፉ የቀይ መስቀል ማህበር ማስረከቡን የእስራኤል መንግስት አረጋግጧል።
ቀሪዎቹን ሁለት እስራኤላውያን ታጋቾች በቀጣይ ለቀይ መስቀል እንደሚያስረክብም ይጠበቃል።
ሃማስ በሶስተኛው ዙር የታጋቾች እና እስረኞች ልውውጥ ስማቸው ያልተጠቀሰ አምስት የታይላንድ ዜግነት ያላቸውን የጥቅምት 7 2023 ታጋቾች እንደሚለቅም ሲኤንኤን ዘግቧል።
እስራኤል በአንጻሩ 110 ፍልስጤማውያን እስረኞችን እንደምትፈታ ተገልጿል።
ከሚለቀቁት ፍልስጤማውያን ውስጥ 32ቱ የእድሜ ልክ እስራት የተላለፈባቸው ናቸው የተባለ ሲሆን፥ 30ዎቹ ደግሞ ህጻናት መሆናቸውን ሃማስ ይፋ አድርጓል።
እስራኤል እና ሃማስ በአሜሪካ፣ ኳታርና ግብጽ አደራዳሪነት በሶስት ምዕራፍ የሚተገበር የተኩስ አቁም ስምምነት መድረሳቸው ይታወሳል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ ሃማስ 33 ታጋቾችን ለመልቀቅ የተስማማ ሲሆን፥ በሁለት ዙሮች ሰባት ታጋቾችን ለእስራኤል አስረክቧል።
እስራኤልም በመጀመሪያው ምዕራፍ 2 ሺህ ፍልስጤማውያን እስረኞችን ለመልቀቅ መስማማቷ የሚታወስ ነው።
የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረበት ጥቅምት 19 2025 አንስቶ ሃማስ ሰባት ሴት ታጋቾችን በሁለት ዙር የለቀቀ ሲሆን፥ እስራኤል ደግሞ 290 ፍልስጤማውያን እስረኞችን ፈታለች።
በመጀመሪያው ምዕራፍ ይለቀቃሉ ከተባሉት 33 ታጋኦች ውስጥ የስምንቱ ህይወት ማለፉን የእስራኤል መንግትስት ቃልአቀባይ ዴቪድ ሜንሰር ባለፈው ሰኞ መግለጻቸው አይዘነጋም።