ባይደን እስካሁን ስልክ አለመደወላቸው የትራምፕ የቅርብ ወዳጅ በሆኑት ኔታንያሁ ደስተኛ አለመሆናቸውን ያሳያል እየተባለ ነው
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር በኢራን እና በፍልስጤም ጉዳዮች ላይ ልዩነቶች መኖራቸውን ቢያምኑም “በጣም ጠንካራ” የስራ ግንኙነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ኋይት ሀውስ ዓርብ በሰጠው መግለጫ ፕሬዝደንት ናይደን እ.ኤ.አ. ጥር 20 ስልጣን ከተረከቡ ወዲህ እስካሁን ባሉት የመጀመሪያ ዙር የስልክ ጥሪዎች ውስጥ ጠ/ሚኒስትር ኔታንያሁን አለማካተታቸው ለሚስተር ኔታንያሁ ትኩረት አለመስጠታቸውን ያሳያል መባሉን አስተባብሏል፡፡
ጠ/ሚኒስትር ኔታንያሁ ለእስራኤል የቻነል 12 የቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት አስተያየት ፕሬዝደንት ባይደን እንዳገለሏቸው የሚነሳውን ሀሳብ ውድቅ በማድረግ “ይደውልልኛል፡፡ የእስራኤል ዲፕሎማሲያዊ ተወካይ ሆኜ ዋሽንግተን ከሄድኩበት ጊዜ አንስቶ እና ባይደን የደላዋር ወጣት ሴናተር ከነበሩበት ጊዜ አንስቶ ለ 40 ዓመታት ያህል በጣም ጠንካራ የወዳጅነት ግንኙነት ነበረን” ብለዋል፡፡
ዴሞክራቲኩ ፕሬዝደንት ባይደን እስካሁን አለመደወላቸው ፣ ከቀድሞው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር የጠበቀ ቅርርብ ባላቸው የእስራኤል ጠ/ሚ ኔታንያሁ ደስተኛ እንዳልሆኑ የሚጠቁም እንደሆነ ይታመናል፡፡ ሚስተር ትራምፕ በ 2017 በዓለ ሲመታቸው ከተፈጸመ ከሁለት ቀናት በኋላ ነበር ለእስራኤል ጠ/ሚኒስትር ስልክ የደወሉላቸው፡፡
ሚስተር ኔታንያሁ “የምንግባባባቸው ብዙ ነገሮች አሉን ፤ ሕብረታችንም በጣም ጠንካራ ነው” ካሉ በኋላ “በኢራን እና በፍልስጤ ጉዳይ ደግሞ ልዩነቶችም አሉን” ብለዋል፡፡
ዋሽንግተን በፕሬዝደንት ትራምፕ ወደተሻረው የኢራን የኑክሌር ስምምነት ከተመለሰች እና ፕሬዝደንት ባይደን በእስራኤል በተያዘው የፍልስጤም መሬት ላይ የእስራኤልን የሰፈራ ግንባታ የሚቃወሙ ከሆነ ጠ/ሚ ኔታንያሁ አለን የሚሉት ህብረት የሚፈተን ይሆናል፡፡
ዘ ናሺናል እንደዘገበው ኋይት ሀውስ ዓርብ ዕለት ባወጣው መግለጫው ሚስተር ባይደን እና ሚስተር ኔታንያሁ በቅርቡ እንደሚያወሩ ቢያሳውቅም ቀኑን ግን አልሰጠም ፡፡