ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ የእስር ማዘዣ እንዲወጣባቸው ጥያቄ መቅረቡን ተቃወሙ
የአለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዋና አቃቤ ካሪም ከሃን በጠቅላይ ሚንስትሩ ላይ የእስር ማዘዣ እንዲወጣ ጥያቄ አቅርበዋል
ኔታንያሁ ውሳኔውን አዲሱ የጸረ ጺወናዊነት ማሳያ ነው ብለዋል
እስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በአለም አቀፉ ፍርድ ቤት የእስር ቤት ማዘዣ እንዲወጣባቸው ጥያቄ መቅረቡን ተቃውመዋል።
የአለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይ ሲ ሲ) ከእሰራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር በተጨማሪ በሶስት የሀማስ ከፍተኛ መሪዎች ላይም የእስር ማዘዣ እንዲያወጣ አቃቤው ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ ማቀረባቸውን ይፋ አድርገዋል።
ኔታንያሁ ውሳኔውን አዲስ የጸረ ጺወናዊነት ማቆጥቆጥ ማሳያ ነው ሲሉ ተቃውመውታል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በበኩላቸው ‘’ኔታንያሁ ከሽብርተኛው ሀማስ መሪዎች ጋር እኩል ለመዳኘት የቀረበው ጥያቄ ያልተገባ ነው’’ ብለውታል፡፡
የአለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዋና አቃቤ ካሪም ከሃን ‘’የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር እና የመከላከያ ሚንስትራቸው ዮአቭ ጋላንት የጦር ወንጀሎችን እና በሰበአዊነት ላይ የሚፈጽሙ ወንጀሎችን ስለመፈጸማቸው የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ’’ ነው ያሉት፡፡
ጉዳዩን ተከትሎ በቴሌቪዥን ቀርበው በቁጣ ምላሽ የሰጡት ኔታንያሁ ‘’ይህ የአዲሱ የጸረ ጺወናዊነት ማሳያ አሳፋሪ ድርጊት ነው’’ ማለቻውን ዩሮ ኒውስ ዘግቧል፡፡
የአለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዋና አቃቤ ካሪም ከሃን ከኔታንያሁ በተጨማሪ በጋዛ የሀማስ መሪ ያህያ ሲነዋር ላይ በተመሳሳይ ክስ የእስር ማዘዣ አውጥቷል፡፡
የኔታንያሁን ቁጣ የተጋሩት የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት ይሳቅ ሄርዞጌ ‘’ከአንድ ፖለቲካዊ ውግንና የተቀዳ፣ በአለምቀፍ ደረጃ የሚገኙ ሽብርተኞችን የልብ ልብ የሚሰጥ፣ ፍርድ ቤቱ የቆመበትን ሜሪት የሚጥስ አሳፋሪ ውሳኔ ነው’’ ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
ደቡብ አፍሪካ፣ ኮሞሮስ ፣ጂቡቲ፣ ቦሊቪያ እና ባንግላዲሽ እስራኤል በጋዛ ፈጸማዋለች ባሉት የዘር ማጥፋት ምርመራ እንዲደረግባት ባሳለፍነው ህዳር መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡
የእስር ማዘዣው ጥያቄ በቴልአቪቭ ሁለት አይነት ተቃራኒ ምላሾችን እያሳተናገደ ነው። በሀማስ የታገቱ እስራኤላዊያንን በቶሎ መፈታትን ሲጠይቁ የነበሩ ዜጎች ኔታንያሁ በቀረበባቸው ክስ መጠየቅ እንደሚገባቸው ጦርነቱንም በስልጣን ላይ ለመቆየት ሆነ ብለው አራዝመውታል ብለው ሲገልጹ፣ ሌሎች ደግሞ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠን መሪ ከሽብርተኛ መሪዎች ጋር እኩል ለፍርድ ቅረብ ማለት ፍትሀዊ አይደለም በሚል ተቃውመውታል፡፡
አይሲሲ የዋና አቃቤውን ጥያቄ ላይ ውሳኔ ለመስጠት የሚሰበሰብ ሲሆን ነገር ግን የእስር ማዘዣውን ከማውጣት ባለፈ ሰዎችን አስሮ ለፍርድ የማቅረብ ስልጣን የለውም፤ ከዚህ ይልቅ አባል ሀገራቱ ማዘዣ የወጣባቸውን ሰዎች አስረው እንዲያቀርቡ ይጠይቃል፡፡
ከዚህ ቀደም በዩክሬን እያደረጉት ባለው ጦርነት የእስር ማዘዣ የወጣባቸው የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የፍርድ ቤቱ አባል ወደ ሆነችው ደቡብ አፍሪካ ሊያደርጉት የነበረውን ጉብኝት መሰረዛቸው ይታወሳል፡፡