አሜሪካ በኔታንያሁ ላይ የእስር ማዛዣ ለማውጣት የሚደረገው ጥረት “አሳፋሪ” ነው አለች
ፕሬዝዳንት ባይደን አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት እስራኤልና ሃማስን በእኩል መመልከት የለበትም ሲሉ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል
አሜሪካ እና እስራኤል 124 አባላት ያሉት የአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት አባል አይደሉም
አሜሪካ አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት በእስራኤል ባለስልጣናት ላይ የእስር ማዘዣ ለማውጣት እያደረገ ያለውን ጥረት አወገዘች።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዋይትሃውስ የአይሁድ አሜሪካውያን ወር ሲከበር ባደረጉት ንግግር፥ የፍርድቤቱን እንቅስቃሴ “አሳፋሪ” ነው ብለውታል።
እስራኤል በጋዛ የምታካሂደው ጦርነት የዜጎቿን ደህንነት ለማስጠበቅ እንጂ የዘር ማጥፋት አልፈጸመችም ሲሉ የተከላከሉት ፕሬዝዳንቱ፥ እስራኤልና ሃማስን በእኩል የተመለከተ ነው ያሉትን የእስር ማዘዣ የማውጣት ጥረት አውግዘውታል።
አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት በአሜሪካ አጋር ሀገር መሪ የእስር ማዘዣ ለማውጣት ሲቃረብ የመጀመሪያው ሲሆን፥ ኔታንያሁን ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና ከቀድሞው የሊቢያ ፕሬዝዳንት ሞአመር ጋዳፊ ጋር ያስቀምጣቸዋል።
የፍርድቤቱ ዋና አቃቤ ህግ ካሪም ካን ያቀረቡትን የእስር ማዘዣ ይውጣ ጥያቄ አሜሪካና እስራኤል እንዲሁም ሃማስ ቢቃወሙትም “ማንም ከህግ በላይ አይደለም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ካሪም ካን ከሲኤንኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ የእስር ማዘዣ እንዲወጣባቸው የተጠየቀባቸው የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የመከላከያ ሚኒስትራቸው ዮቭ ጋላንት በጋዛ የጦር ወንጀል መፈጸማቸውን አንስተዋል።
የሃማስ የፖለቲካ መሪው ኢስማኤል ሃኒየህ፣ በጋዛ የሃማስ የፖለቲካ ክንፍ ሃላፊው ያህያ ሲንዋር እና የቡድኑ ጦር አዛዥ መሀመድ አል ማስሪም በተመሳሳይ በጦር ወንጀል እና በሰብአዊነት ላይ በሚፈጸም ወንጀል የእስር ማዘዣ እንዲወጣባቸው ተጠይቋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት ዋና አቃቤ ህግ ካሪም ካንን “በዘመናችን ጸረሴማዊነት የተጸናወታቸው ሰው” ናቸው ሲሉ ተደምጠዋል።
ሃማስ በበኩሉ “ተጎጂን ከገዳይ ጋር አመሳስለዋል” ያላቸውን ካሪም ካን በቡድኑ አመራሮች ላይ ያቀረቡትን የእስር ማዘዣ እንዲሰርዙ አሳስቧል።
ከ35 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ያለቁበትን የጋዛ ጦርነት በመሩ የእስራኤል ባለስልጣናት ላይ የእስር ማዘዣውን ለማውጣት ሰባት ወራት መጠበቅ እንዳልነበረባቸውም በማንሳት።
እስራኤልም ሆነች አሜሪካ 124 አባል ሀገራት ያሉት የአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት አባል አይደሉም።
ይሁን እንጂ ፍርድቤቱ ዋና አቃቤ ህጉ ያቀረቡትን ጥያቄ የሚያጸድቀው ከሆነ ኔታንያሁ ወይም የመከላከያ ሚኒስትራቸው ብሪታንያ እና ጀርመንን ጨምሮ ወደ 124 የፍርድቤቱ አባል ሀገራት መጓዝ አይችሉም።
የፍርድቤቱን መመስረቻ የፈረሙት ሀገራት የእስር ማዘዣ የወጣባቸውን ሰዎች አሳልፈው የመስጠት ግዴታ አለባቸው።
አሜሪካ በዩክሬን እና ጋዛ ጦርነት የአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት ሚና ዙሪያ ሁለት አይነት አቋም ይዛለች።
ዋሽንግተን ፍርድቤቱ ሞስኮ በዩክሬን የምትፈጽመውን የጦር ወንጀል በጥብቅ እንዲከታተል ስትወተውት ቆይታ በፕሬዝዳንት ፑቲን ላይ የእስር ማዘዣ ማውጣቱንም አድንቃ ነበር።
የጥቅምት 7ቱን የሃማስ ጥቃት ተከትሎ ወደ ጋዛ የገባችው እስራኤል ፍልስጤማውያን ላይ የምታደርሰውን በደል ግን ፍርድቤቱ እንዲመለከተውም ሆነ በኔታንያሁ ላይ የእስር ማዘዣ እንዲያወጣ አልፈለገችም።