ኔታንያሁ ወታደሮችን ከጋዛ በማስወጣት ዙርያ ከሀገራቸው ተደራዳሪዎች ጋር መጋጨታቸው ተነገረ
እስራኤልን የወክሉት ተደራዳሪዎች ጠቅላይ ሚንስትሩ በድንበሮች ዙርያ በሚያሳዩት “ግትር” አቋም ተቃውሟቸውን እየገለጹ ነው ተብሏል
ኔታንያሁ በጦርነቱ ዙርያ “ፍጹም አሸናፊነትን” መፈለጋቸው ግጭቱ እንዲራዘም ምክንያት ስለመሆኑ ተነግሯል
ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የእስራኤል ወታደሮች ከሁለት የጋዛ ድንበር አካባቢዎች አይወጡም በሚለው አቋማቸው ከገዛ ተደራዳሪ ልኡኮቻቸው ጋር ቅራኔ ውስጥ እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡
ኔታንያሁ ጋዛን ከግብጽ ጋር ከሚያዋስነው “ፊላዴልፊያ” ድንበር እና የጋዛ ሰርጥን ለሁለት ከሚከፍለው “ናትዛሪም” የድንበር ስፍራ የእስራኤል ወታደሮች አይወጣም በሚለው አቋማቸው የተነሳ የድርድር ሂደቱ እየተጓተተ እንደሚገኝ ነው የተሰማው፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ እነኚህን አካባቢዎች አለቅም ያሉበት ምክንያት ሀማስ የጦር መሳርያዎችን ወደ ማዕከላዊ ጋዛ የሚያስገባባቸው መተላለፍያዎች ናቸው በሚል ነው፡፡
በተጨማሪም ቴልአቪቭ በአካባቢዎቹ ላይ የፍተሸ ኬላዎችን በማቋቋም ታጣቂዎች ከደቡባዊ አካባቢዎች ወደ ሰሜናዊ ጋዛ ሰርጥ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ መቆጣጠር ትፈልጋለች ተብሏል፡፡
ሮይተርስ ከእስራኤል ተደራዳሪዎች አንዱ እንደሆኑ ከጠቀሳቸው የውስጥ ምንጭ አገኝሁት ባለው መረጃ መሰረት ልኡካኑ እና ኔታንያሁ በነዚህ የድንበር አካባቢዎች ቀጣይ እጣ ፈንታ ዙርያ ከፍተኛ የሀሳብ ልዩነት ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ ከድንበሮቹ አካባቢ ጥቂት 100 ሜትሮችን ወደ ኋላ ለማፈግፈግ ፈቃደኛ ቢሆኑም ሙሉ ለሙሉ አካባቢውን መልቀቅ በእስራኤል ላይ ድጋሚ ጥቃት ያስከትላል ብለው እንደሚምኑ ነው የተነገረው፡፡
በሞሳድ የደህንነት አገልግሎት ዋና ሃላፊ ዴቪድ ባርኒያ የሚመራው በኳታር እና ካይሮ ድርድር እያካሄደ የሚገኘው ልዑክ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተኩስ አቁም ስምምነቱ እንዳይፈረም እንቅፋት ከሆነው አቋማቸው እንዲለሳለሱ መጠየቁን ሮይተርስ በዘገባው አካቷል፡፡
ኔታንታሁ በበኩላቸው “ተደራዳሪ ቡድኑ የእስራኤልን የደህንነት ጥያቄ አደጋ ውስጥ ሊከት በሚችል ሀሳብ ለመስማማት ዝግጁ ሆኗል” ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
የጋዛውን ጦርነት ማስቆም ከፖለቲካ ጥቅማቸው አንጻር እያሰሉ ይገኛሉ በሚል ተደራራቢ ጫና እየደረሰባቸው የሚገኙት ኔታንያሁ በጦርነቱ ዙርያ “ፍጹም አሸናፊነትን” መተለማቸው ግጭቱ እንዲራዘም ምክንያት ስለመሆኑ ይነገራል፡፡