የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር የመከላከያ ሚኒስትሩን ከሃላፊነት አነሱ
ሚኒስትሩ ዮቭ ጋላንት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የፍትህ ስርአቱን ለማሻሻል ያቀረቡትን ህግ በተቃወሙ ማግስት ነው ከስራቸው የተባረሩት
ለመንግስት ዳኞችን የመምረጥና የከፍተኛ ፍርድቤት ስልጣንን የመቀነስ ስልጣን ማሻሻይ ተቃውሞው በርክቶበታል
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የሀገሪቱን የመከላከያ ሚኒስትር ከሃላፊነት ማንሳታቸው ተነገረ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅህፈት ቤት የመከላከያ ሚኒስትሩ ዮቭ ጋላንት ከሃላፊነታቸው መነሳታቸውን አስታውቋል።
ይሁን እንጂ መግለጫው ሚኒስትሩ ከስራ የተሰናበቱበትን ምክንያት አልጠቀሰም።
የኔታንያሁ ሊኩድ ፓርቲ አባል የነበሩትና የቀድሞው ጀነራል ከሰሞኑ በቴሌቪዥን የሰጡት አስተያየት ግን ለስንብታቸው ምክንያት እንደሚሆን ሬውተርስ ዘግቧል።
ሚኒስትሩ የእስራኤል ፓርላማ (ክኔሴት) እንዲያፀድቀው በኔታንያሁ የቀረበውን የፍትህ ስርአቱን ያሻሽላል የተባለው ህግ በመላ ሀገሪቱ ተቃውሞ ማስነሳቱን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማሻሻያውን ለጊዜው እንዲያዘገዩት በመጠየቅና ተቃውሟቸውን በማሰማትም ቀዳሚው ናቸው።
ዮቭ ጋላንት ከስልጣን መነሳታቸው እንደተነገረ በኒውዮርክ የእስራኤል ቆንፅላ ጀነራል አሳፍ ዛሚር በፈቃዳቸው ስራቸውን መልቀቃቸውን ይፋ አድርገዋል።
ማሻሻያው ለመንግስት ዳኞችን የመምረጥና የከፍተኛ ፍርድቤት ስልጣንን የመቀነስ ስልጣን ይሰጣል ተብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ማሻሻያው የፍትህ ተቋማትን ከፍ ያለ ጣልቃገብነት በመቀነስ የህግ አስፈፃሚ እና ተርጓሚውን ስልጣን ሚዛናዊ ያደርጋል ብለዋል።
ተቃዋሚዎች ግን ህጉ ቀኝ ዘመሙ ጥምር መንግስት የስልጣን ክፍፍልን በመናድ ወደ አምባገነንነት እያንደረደረው ነው እያሉ ነው።
የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎቹ የር ላፒድ እና ቤኒ ጋንዝ የሊኩድ ፓርቲ አባላት ይህን ህግ እንዳያፀድቁ የጠየቁበትን መግለጫ አውጥተዋል።
ቴል አቪቭን ጨምሮ በበርካታ የእስራኤል ከተሞች ማሻሻያውን የተቃወሙ ሰልፈኞች አደባባይ ወጥተዋል ብሏል አሶሼትድ ፕረስ በዘገባው።