አዲሱ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ “አዲስ ጥምር መንግስት መስርቻለሁ” አሉ
የኔታኒያሁ ሊኩድ ፓርቲ እና አጋሮቹ በህዳሩ ምርጫ ከፓርላማው 120 መቀመጫዎች 64ቱን ይዘዋል
ኔታኒያሁ አዲሱን መንግስት ለመመስረት ከቀኝ አክራሪ አጋሮች ጋር ለሳምንታት ተደራድረዋል ነው የተባለው
አዲሱ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ባለፈው ወር በተካሄደው ምርጫ የሊኩድ ፓርቲ እና አጋሮቻቸው አብላጫ ድምጽ ካገኙ በኋላ አዲስ መንግስት መመስረታቸውን ተናግረዋል።
እስራኤላውያን በአራት ዓመታት ውስጥ ለአምስተኛ ጊዜ በፈረንጆቹ ህዳር 1 ቀን 2022 ምርጫ አካሂደዋል። የኔታኒያሁ ጥምረት 120 አባላት ካሉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ 64 መቀመጫዎችን አሸንፏል።
ኔታንያሁ በትዊተር ገጻቸው "ባለፈው ምርጫ ለተደረገልን ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ ምስጋና ይግባውና ለሁሉም የእስራኤል ዜጎች የሚጠቅም መንግስት ማቋቋም ችያለሁ" ብለዋል።
በፈረንጆቹ ጥር 2021 በሙስና ምርመራ ከስልጣን ከመባረራቸው በፊት ኔታኒያሁ ለ15 ዓመታት የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው አገልግለዋል።
አዲሱን መንግስት ለመመስረት ከቀኝ አክራሪ አጋሮች ጋር ለሳምንታት ተደራድረዋል ነው የተባለው።
የኔታንያሁ የካቢኔ አባላት የደህንነት ሚንስትር ሆነው የሚሾሙትንና የብሔራዊ ፖሊስ ኃይልን የሚመሩን ኢታማር ቤን-ጊቪርን ይጨምራል ሲል ፎክስ ኒውስ ዘግቧል።
የፋይናንስ ሚንስትር ሆነው የሚያገለግሉት የዌስት ባንክ ሰፈራ መሪ የነበሩት ቤዛል ስሞትሪክ ናቸው የተባለ ሲሆን፤ አቪ ማኦዝ የእስራኤልን የትምህርት ስርዓት ይመራሉ ተብሏል።
በኢራን ስምምነት እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ከኔታንያሁ ጋር ከፍተኛ ልዩነት ያለው የባይደን አስተዳደር ከአዲሱ መንግስት ጋር በቅርበት ለመስራት ቃል ገብቷል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ "መንግስትን ከግለሰባዊ ስብዕናዎች ይልቅ በሚከተላቸው ፖሊሲዎች እንለካለን።
ባለፉት ሰባት አስርት ዓመታት ውስጥ በግንኙነታችን ውስጥ ካስቀመጥነው የጋራ መመዘኛዎች ጋር እናያለን” ሲሉ ስለ እስራኤል አዲስ መንግስት ተናግረዋል።