ኔታንያሁ ታጋቾችን ለማስለቀቅ ከሃማስ ጋር ድርድር እየተካሄደ መሆኑን ፍንጭ ሰጡ
ከሃማስ ጋር የሚፈረም የትኛውም ስምምነት እየተወሰደበት ያለው ወታደራዊ እርምጃ ውጤት ነው ሲሉም ተናግረዋል
አሜሪካ እና ኳታር በሃማስ የታገቱ ሰዎችን ለማስለቀቅ ጥረት እያደረጉ ነው ተብሏል
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ታጋቾችን ለማስለቀቅ ከሃማስ ጋር ድርድር እየተካሄደ መሆኑን ፍንጭ ሰጡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአሜሪካው ኤንቢሲ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ “ስምምነት ሊኖር ይችላል (ከሃማስ ጋር)፣ ይሁን እንጂ ስለዚህ ጉዳይ ብዙ ካላወራው የሚሳካበትን መንገድ ይበልጥ ገፍቼበታለሁ ማለት ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።
እስራኤል በጋዛ ሰርጥ እየወሰደችው ያለው እርምጃ መጠናከር ሃማስ ታጋቾችን እንዲለቅ ያስገድደዋልም ነው ያሉት።
ኔታንያሁ ከሃማስ ጋር ስለሚደረገው ስምምነት ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥበዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ጃክ ሱሊቫኒ በበኩላቸው ታጋቾችን ለማስለቀቅ የሚያስችል ስምምነት ላይ ለመድረስ ድርድር እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
“ንግግሩ ውስብስብ እና አስቸጋሪ በመሆኑ ዝርዝር መረጃ መስጠት አልችልም” ማለታቸውንም አናዶሉ አስነብቧል።
ዋይትሃውስም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የኳታሩ ኢሚር ሼክ ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ በጋዛ ወቅታዊ ሁኔታ መምከራቸውን ገልጿል።
መሪዎቹ በትናንትናው እለት ባደረጉት የስልክ ውይይት የታገቱ ሰዎች በፍጥነት እንዲለቀቁ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ነው የጠቀሰው።
ኳታር ታጋቾቹ በሚለቀቁበት ሁኔታ ዙሪያ እስራኤልና ሃማስን በማደራደር ላይ ትገኛለች።
ሃማስ ያገታቸውን ሰዎች ለመልቀቅ ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ስለመሟላታቸውም ሆነ አሜሪካ እና ኳታር ስለገለጹት የድርድር መረጃ ምላሽ አልሰጠም።
ቡድኑ የጋዛው ድብደባ ካልቆመና በእስራኤል እስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ፍልስጤማውያን ካልተለቀቁ የታገቱ ሰዎችን አለቅም ማለቱ የሚታወስ ነው።