አሜሪካ ለእስራኤል 147 ሚሊየን ዶላር የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎችን ለመሸጥ ወሰነች
ዋሽንግተን በኮንግረንሱ ሳታጸድቅ ለቴል አቪቭ አስቸኳይ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ስትፈቅድ የትናንቱ ለሁለተኛ ጊዜ ነው
12ኛ ሳምንቱን በያዘው የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ህይወታቸው ያለፈ ፍልስጤማውያን ቁጥር 21 ሺህ 507 ደርሷል
አሜሪካ ለእስራኤል 147 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር የሚያወጡ የታንክ ተተኳሾችን ለመሸጥ ወሰነች።
ፔንታጎን “አስቸኳይ” የሽያጭ ውሉን ያጸደቀው የኮንግረንሱን ይሁንታ ሳይጠቅይ ነው።
“ውሳኔው በኮንግረንሱ ለማጸደቅ የሚወስደውን ጊዜ በማሳጠር ለእስራኤል በፍጥነት ለመድረስ ያስችላል” ብለዋል የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን።
ዋሽንግተን አለማቀፉን የሰብአዊ መብት እና የጦርነት ህግ መሰረት በማድረግ ለአጋሯ ቴል አቪቭ የጦር መሳሪያ ሽያጯን እንደምትቀጥልም መናገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
የባይደን አስተዳደር ባለፈው ወርም በተመሳሳይ ኮንግረንሱን ሳያጸድቅ 45 ሺህ የታንክ ተተኳሾችን ለእስራኤል ለመሸጥ መወሰኑ ይታወሳል።
ይህም ሀገሪቱ እስራኤል በጋዛ በንጹሃን ላይ የምትፈጽመውን ድብደባ እንድትቀንስ ከምታደርገው ጫና ጋር የሚቃረን ነው በሚል ተቃውሞ ሲነሳበት ይደመጣል።
ፔንታጎን በበኩሉ አሜሪካ ለእስራኤል ስለምትሸጠው የጦር መሳሪያ የተቀመጠ ቅድመሁኔታ አለመኖሩንና የዋሽንግተንን ብሄራዊ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ይቀጥላል በሚለው አቋሙ ጸንቷል።
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ግን የዋሽንግተን የጦር አምሳሪያ ሽያጭ በጋዛ በአየርና በምድር ድብደባዋን ለቀጠለችው እስራኤል ተጨማሪ ሃይል የሚፈጥርና የንጹሃንን ህልፈት የሚጨምር ነው እያሉ ነው።
12ኛ ሳምንቱን በያዘው የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ህይወታቸው ያለፈ ፍልስጤማውያን ቁጥር 21 ሺህ 507 መድረሱን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፤ ይህም ከጋዛ ነዋሪዎች 1 በመቶ እንደሚሆን ተነግሯል።
እስራኤል በትናንትናው እለት ብቻ በካን ዩኒስ በፈጸመችው ጥቃት የ200 ፍልስጤማውያን ህይወት መቀጠፉ ነው የተገለጸው።