በኢትዮጵያ በቀጣዮቹ 10 ቀናት የሚኖረው የዝናብ ሁኔታ ምን ይመስላል፤ አስጊነቱስ ምን ያክል ነው?
የኢትዮጰያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት መጠኑ ከፍ ያለ ዝናብ ስለሚኖር ጥንቃቄ እንዲደረግ መልዕክት አስተላልፏል
በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች በ24 ሰዓት ውስጥ ከ30 ሚሊ ሜትር በላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ይኖራል
በኢትዮጵያ በቀጣዮቹ 10 ቀናት መጠኑ ከፍ ያለ ዝናብ ስለሚኖር ጥንቃቄ እንዲደረግ የኢትዮጰያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት መልዕክት አስተላልፏል።
የኢትዮጰያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዛሬ ባወጣው መረጃ በሚቀጥሉት 10 ቀናት በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የዝናብ መጠን ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስቧል
ኢንስቲትዩቱ በመካካለኛው፣ በምዕራብ፣ በደቡብ ምዕራብ እንዲሁም በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ጠንካራ እና የተስፋፋ የዝናብ መጠንና ስርጭት እንደሚኖር ባወጣው መግለጫው አስታውቋል።
በመካከለኛው፣ በሰሜን ምዕራብ፣ በምዕራብ እና በደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች በ24 ሰዓት ውስጥ ከ30 ሚሊ ሜትር በላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ይኖራል ሲል ማስጠንቀቂያ አዘል መልክቱን አስተላልፏል።
በመሆኑም በሚቀጥሉ ቀናት ከመደበኛ በላይ የዝናብ መጠንና ስርጭት ይኖራል ያለው ኢንስቲቲዩቱ፤ ይህም ሁኔታ የጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ተጽዕኖ እንዳይደርስ አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄና ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።
አካባቢዎቹ አልፎ አልፎ በፀሐይ ኃይል ታግዞ ከሚፈጠሩ ደመና ክምችቶች ጋር ተያይዞ ነጎድጓዳማ ዝናብ እንደሚኖራቸው ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።
በመደበኛ ሁኔታ በቀጣዮቹ 10 ቀናት የክረምቱ ዝናብ በስርጭትም ሆነ በመጠን ከምሥራቅ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች ቀስ በቀስ የመቀነስ አዝማሚያ እንደሚያሳይ ኢንስቲትዩቱ ባወጣው መግለጫው አጋርቷል።
በኢትዮጵያ የክርመቱን ወቅት ተከትሎ እየጣለ ባለው ከባድ ዝናብ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አጋዎችን በማስከተል ላይ ይገኛል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ የ250 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።
በቅርቡም በአማራ ከልል ሰሜን ጎንደር ዞን አራት ወረዳዎች ከሰሞኑ በደረሱ የመሬት መንሸራተት አደጋዎች የሞቱ ሰዎች ቁጥር 23 እንደደረሰም ተነግሯል።
በወላይታ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ የ11 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፤ በሲዳማ ክልል በመሬት መንሸራተት አደጋ የ6 ሰዎች ህይወት አልፏል።
በተጨሪም ሰልጤ ዞንን ጨምሮ በተለያየ የሀገሪቱ አካባዎች ባጋጠሙ የጎርፍ አደጋዎች በርካቶች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።