የአሜሪካ ማዕከላዊ እዝ ሀውቲዎች ሁለቱን መርከቦች በሁለት ሚሳይሎች እና ድሮን ኢላማ ማድረጋቸውን እና መምታታቸውን ገልጿል
የሀውቲ ታጣቂዎች ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን ማጥቃታቸውን የአሜሪካ ጦር ገለጸ።
የአሜሪካ ጦር በኢራን የሚደገፉት የሀውቲ ታጣቂዎች ሁለት ድፍድፍ ነዳጅ የጫኑ መርከቦችን በትናንትናው እለት በቀይ ባህር ላይ አጥቅተዋል ብሏል።
ጦሩ እንደገለጸው ከሆነ ጥቃት የደረሰባቸው መርከቦች የሳኡዲ ሰንደቅ አላማ ስታውለበልብ የነበረችው አምጃድ እና የፓናማ ሰንደቅአላማ ስታውለበለብ የነበረችው ብሉ ላጉን ናቸው።
ሀውቲዎች ሰኞ ምሽት ብሉ ላጉንን በበርካታ ድሮኖች እና ሚሳይሎች ማጥቃታቸውን ያመኑ ሲሆን ስለሳኡዲ መርከብ ጉዳይ ግን ምንም ያሉት ነገር የለም።
የአሜሪካ ማዕከላዊ እዝ ሀውቲዎች ሁለቱን መርከቦች በሁለት ሚሳይሎች እና ድሮን ኢላማ ማድረጋቸውን እና መምታታቸውን ገልጿል።
ሁለቱም መርከቦች ነዳጅ ጭነው ነበር ያለው የአሜሪካ ጦር መግለጫ ጥቃቱን "ሀውቲዎች የፈጸሙት ኃላፊነት የጎደለው የሽብር ድርጊት" ሲል ገልጾታል። ሮይተርስ ሁለት ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው መርከቦቹ በሚመቱበት ወቅት ተቀራርበው ሲጓዙ ነበር። የደረሰው ጥቃት ቀላል በመሆኑ መርከቦቹ ጉዟቸውን መቀጠላቸውም ተገልጿል።
ሁለት ሚሊዮን በርሜል ድፍድር ነዳጅ የጫነችው የሳኡዲዋ አምጃድ መርከብ ባለቤት የሆነው ሳኡዲ ናሽናል ሺፒንግ ግሩፕ ባህሪ ስለጉዳዩ አስተያየት አለመስጠቱን ዘገባው ጠቅሷል።
ብሉ ላጉን የሚያስተዳድረው የግሪኩ አስተዳዳሪ ሲ ትሬድ ማሪን ኤስኤ በተመሳሳይ ስለጉዳዩ መልስ አልሰጠም። የሱዝማዝ ታንከሯ የመጨረሻ የመጫን አቅሟ አንድ ሚሊዮን መርሜል ነዳጅ እንደሚሆን ተገልጿል።
የሳኡዲዋ መርከብ በቀጥታ ኢላማ ተደርጋለ ላይሆን እንደሚችል ዘገባው ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል። የአለም ትልቋ ነዳጅ አምራች ሳኡዲ አረቢያ ሀውቲዎች መርከቦችን ኢላማ ለማድረግ በግዛቷ ላይ ሲተኩሱ በከፍተኛ ጥንቃቄ እየተመለከተቻቸው ነው። ሳኡዲ አረቢያ ምስቅልቅል ካስከተለው የየመን ጦርነት ራሷን ለመነጠል እየሞከረችም ነው።
የሀውቲ ታጣቂዎች በቀይ ባህር እና በኤደን ባህር ሰላጤ በሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ ከባለፈው ህዳር ወር ጀምረው ጥቃት እያደረሱ ያሉት ከእስራኤል ጋር እየተዋጋ ላለው ሀማስ አጋርነት ለማሳየት ነው ማለታቸው ይታወሳል። ሀውቲዎች እስካሁን በፈጸሟቸው ጥቃቶች የሰጠሙ መርከቦችም አሉ።
ሀውቲዎች ይህን ጥቃት የማያቆሙት በጋዛ ተኩስ ሲቆም ነው ብለዋል።
አሜሪካ እና አጋሮቿ ሀውቲዎች እያደረሱት ያለውን ጥቃት ለማስቆም የመን ውስጥ ዘልቀው በመግባት የሀውቲ ይዞታዎች ቢደበድቡም፣ ጥቃቱን ማስቆም አልቻሉም።