ፍልስጤማውያንን ከምድራቸው የማስወጣት የትኛውንም ሙከራ እቃወማለሁ - ሳኡዲ
ሪያድ ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የምጀምረው ፍልስጤም የተባለች ሀገር ስትመሰረት ብቻ ነው ብላለች
ትራምፕ አሜሪካ የጋዛ ሰርጥን መጠቅለል ትፈልጋለች ማለታቸው በአረብ ሀገራት ውግዘት አስከትሎባቸዋል
ሳኡዲ አረቢያ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት የምጀምረው የፍልስጤም ነጻ ሀገርነት ሲረጋገጥ ብቻ ነው አለች።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያቀረቡትን ጋዛን የመጠቅለል እቅድም ተቃውማለች።
የሳኡዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ ፍልስጤማውያንን ከራሳቸው መሬት የማፈናቀል የትኛውንም ሙከራ እንደማይቀበለው ጠቁሟል።
መግለጫው ሳኡዲ በፍልስጤማውያን ዙሪያ የያዘችው አቋም ለድርድር የሚቀርብ አለመሆኑንም ነው ያመላከተው።
የሳኡዲ ልኡል አልጋወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን ሪያድ የያዘችው አቋም በየትኛውም ሁኔታ ትርጓሜው የማይለዋወጥና ግልጽ መሆኑን ማረጋገጣቸውንም አብራርቷል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር በዋይትሃውስ በሰጡት መግለጫ "አሜሪካ የጋዛ ሰርጥን ትጠቀልላለች" የሚል አስደንጋጭ ንግግር አድርገዋል።
"ጋዛን የእኛ ካደረግን በኋላ ያልፈነዱ አደገኛ ቦምቦችንና ሌሎች መሳሪያዎችን እናከሽፋለን፣ የፈራረሰውን ቦታ አስተካክለን ብዙ የስራ ዕድል እንፈጥራለን፤ በአካባቢው ላሉ ሰዎች መኖሪያ የሚሆን ቤት በመገንባት ኢኮኖሚያዊ ልማት እናካሂዳለን" ማለታቸውም ፍልስጤማውያንን አስቆጥቷል።
ትራምፕ ከባለፈው ወር መጨረሻ ጀምሮ የፈራረሰችው ጋዛ እስክትጸዳ ድረስ ግብጽና ዮርዳኖስ ፍልስጤማውያንን እንዲያያስጠልሉ ያቀረቡት ሃሳብ በሀገራቱ ተቀባይነት አላገኘም።
በትናንቱ የዋይትሃውስ ንግግራቸው ጋዛን የመቆጣጠር እቅዳቸውን ለሳኡዲ ሲያቀርቡ ተቃውሞ እንዳልገጠማቸው ቢያነሱም ሪያድ ያወጣችው መግለጫ ከዚህ ይቃረናል።
አሜሪካ የመካከለኛው ምስራቅ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገር ሳኡዲ አረቢያ ከእስራኤል ጋር ግንኙነቷን እንድታድስ እና ለቴል አቪቭ ሀገርነት እውቅና እንድትሰጥ ወራት የፈጀ የዲፕሎማሲ ጥረት አድርጋለች።
የሪያድና ቴል አቪቭ ግንኙነትን የማደስ ሂደት ግን በጥቅምት ወር 2023 በጋዛ በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት መጓተቱ ይታወሳል።