ከኦባማ ጋር በተደጋጋሚ ቃላት የተወራወሩት ኔታንያሁ ለጆ ባይደንስ ምን ምላሽ ሰጡ?
ኔታንያሁ ለባይደን የፍትህ ስርአት ማሻሻያውን አቁሙት ጥያቄ፥ “እስራኤል የውስጥ ጉዳዩዋን ራሷ ትወስናለች እንጂ ለውጭ ጫና እጅ አትሰጥም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል
በእስራኤል ይደረጋል የተባለው የፍትህ ስርአት ማሻሻያ ለሁለት ሳምንት የዘለቀ ተቃውሞ አስነስቷል
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የፍትህ ስርአቱን ለማሻሻል የያዙትን እቅድ እንዲሰርዙ በአሜሪካው ፕሬዝዳንት የቀረበላቸውን ጥያቄ ውድቅ አደረጉ።
“እስራኤል ሉአላዊ ሀገር ናት፤ የውስጥ ጉዳዩዋን በራሷ ህዝብ ፍላጎት እንጂ ከውጭ ሀገር በሚመጣ (ከወዳጅም ጭምር) ጫና አትወስንም” ብለዋል ኔታንያሁ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ምላሻቸው “የማይናወጥ” ነው ያሉትን የአሜሪካ እና እስራኤል ግንኙነት እንደማያሻክረው በመግለጽም ነገሩን ለማብረድ ጥረት ማድረጋቸውን ነው አሶሼትድ ፕረስ የዘገበው።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ትናንት ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ፥ ኔታንያሁ ለሁለት ሳምንታት እስራኤልን በተቃውሞ ያናወጠውን የፍትህ ስርአት ማሻሻያ ወደጎን እንዲተውት ጠይቀው ነበር።
በቅርቡም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ዋይትሃውስ ዘልቀው በጉዳዩ ላይ ለመምከር መታሰቡን የዋይትሃውስ ባለስልጣናት ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ኔታንያሁ ዛሬ በትዊተር ገጻቸው ያስተላለፉት መልዕክት የሚለወጥ ነገር የለም የሚል ይዘት ያለው ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቅርብ ሰውና የፖሊስ አዛዡ ኢታማር ቤን ግቪር፥ “እስራኤል በአሜሪካ ሰንደቅ ላይ ካሉት ከዋክብት አንዷ አይደለችም” ሲሉ መደመጣቸውም የቃላት ጦርነቱ ስለመቀጠሉ ማሳያ ሆኗል።
ኔታንያሁ ከአሜሪካ መሪዎች ጋር ቃላት ሲወራወሩ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ጋር በፍልስጤማውያን ጉዳይ እና በ2015ቱ የኢራን ኒዩክሌር ስምምነት ዙሪያ በተደጋጋሚ ሰጣገባ ውስጥ መግባታቸው ይታወሳል።
ኔታንያሁ የመሰረቱት ጥምር መንግስት አደርገዋለሁ ያለው የፍትህ ስርአት ማሻሻያም የሁለቱ ወዳጅ ሀገራት መሪዎች የንትርክ መንስኤ ሆኗል።
ማሻሻያው በሙስና የሚጠረጠሩት ጠቅላይ ሚኒስትር) ዳኞችን የመሾም የመጨረሻ ስልጣን እንዲኖራቸው ያደርጋል።
ሊኩድ ፓርቲና አጣማሪዎቹ የተቆጣጠሩት ምክርቤት (ክኔሴት) የሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ እንዲሽርም ስልጣን የሚስጥ ነው ተብሏል።
የዳኞችን “ያልተገባ ጣልቃገብነት” ይቀንሳል በሚል በኔታንያሁ የቀረበው የፍትህ ስርአቱ ማሻሻያ፥ ከተጠያቂነት ለማምለጥ የተሸረበ ነው፤ ሀገሪቱንም ወደለየለት አምባገነናዊ ስርአት ይወስዳታል ያሉ እስራኤላውያንም በአደባባይ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ሰንብተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማሻሻያውን ለጊዜው እንዲቆም አድርጌዋለሁ ቢሉም ዛሬ ለባይደን ጥያቄ የሰጡት ምላሽ ግን ዳግም ተቃውሞን የሚቀሰቅስ እንዳይሆን ተሰግቷል።