በሱዳን ጦርነት የሞቱ ንጹሀን በጋዛ ከተገደሉት እንደሚበልጥ ጥናት አረጋገጠ
በ14 ወራቱ ጦርነት 61 ሺህ የሚጠጉ ንጹሀን መሞታቸውን የብሪታንያ እና ሱዳን አጥኚዎች ገልጸዋል
በርካቶቹ ሟቾች ከጦርነቱ ባለፈ በርሀብ እና በበሽታ ህይወታቸው ማለፉ ነው የተነገረው
በሱዳን ጀነራሎች ጦርነት የሟቾች ቁጥር አሁን ላይ ተመዝግቦ ከሚገኘው ሊበልጥ እንደሚችል ጥናት አመላከተ፡፡
በለንደን የንጽህና እና የትሮፒካል ህክምና ማዕከል እና በሱዳን ጥናትና ምርምር ቡድን የተደረገው ጥናት በ14 ወራቱ ጦርነት ከ61 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን አመላክቷል። የሟቾች ቁጥር በጋዛ እየተካሄደ በሚገኘው ጦርነት ከሞቱት ሰዎች እንደሚልቅም በመጥቀስ።
ከጦርነቱ ባሻገር የረሃብ እና በሽታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣት ዋነኛ የሞት መንስኤዎች መሆናቸውንም ነው ጥናቱ የጠቆመው፡፡
የተባበሩት መንግስታት እና ሱዳን በጦርነቱ 26 ሺ ሰዎች መሞታቸውን በተለያየ ጊዜ ባወጡት መግለጫ መግለጻቸው ይታወሳል። አዲሱ ጥናት አሃዙን ወደ 61 ሺህ ከፍ ያደረገው ሲሆን፥ ይህም መጠን በሱዳን የሚገኘውን አሳሳቢ ሰብአዊ ሁኔታ አመለካች ነው ተብሏል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግጭቱ 11 ሚሊዮን ሰዎችን ከቤት ንብረታቸው እንዳፈናቀላቸው እና በዓለም ላይ ትልቁን የረሃብ ቀውስ እንዳስከተለ ገልጿል።
በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ በተከሰተው ረሃብ ወደ 25 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ወይም ከሱዳን ግማሽ ያህሉ ህዝብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው መግለጹ አይዘነጋም፡፡
በሱዳን የሞቱ ሰዎችን መቁጠር ፈታኝ ሆኖ ቆይቷል የሚለው አዲሱ ጥናት በሰላም ጊዜም ቢሆን በሀገሪቱ የሟቾች ቁጥር በተገቢው ሁኔታ አለመሰነዱን አብራርቷል።
ጦርነቱ እየበረታ በሄደ ቁጥር የሰዎች ሞት ከሚመዘገብባቸው ቦታዎች፣ ሆስፒታሎች፣ የአስክሬን ክፍሎች እና የመቃብር ስፍራዎች ተቆጥረዋል።
የኢንተርኔት እና የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት መቋረጥ ሚሊዮኖች ከውጭው ዓለም ጋር እንዳይገኛኙ አድርጓቸዋል፡፡
አጥኚዎቹ ከሟቾቹ መካከል 7 በመቶ የሚሆኑት ሆነ ተብሎ በተፈጸመ ጥቃት መገደላቸውን ያረጋገጡ ሲሆን፥ ግኝቶቹ በጦርነት የተጎዱ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ተመሳሳይ ወይም የከፋ ጉዳት ሊደርስባቸው እንደሚችል ጠቅሰዋል፡፡
ጥናቱ በካርቱም ግዛት በአሜሪካ የትጥቅ ግጭት ሁነቶች እና ቦታዎች ምዝገባ (ኤሲኤልኢዲ) ከተመዘገበው 20 ሺ 178 የሟቾች ቁጥር በእጥፍ እንደሚበልጥ አመላክቷል፡፡
የተጠቀሰውን የሟቾች ቁጥር ንጽጽር ለመስራት ሶስት አይነት የጥናት መንገዶችን መጠቀማቸውን የገለጹት አጥኚዎቹ፤ በሀገሪቱ ያለው የሰላም ሁኔታ በርካታ ቦታዎች ላይ እንዳይደርሱ በማድረጉ እንዲሁም በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ ሰዎች የተቀበሩበት ሁኔታ ለመቁጠር አመቺ ባለመሆኑ የሟቾች ቁጥር ከዚህ በላይም ሊያሻቅብ ይችላል ብለዋል፡፡
በምግብ እጥረት እንዲሁም በወባ ፣ ኮሌራ እና የደንጌ በሽታዎች ተይዘው የህክምና አገልግሎት ለማግኘት የሚጠባበቁ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ መሆን የሟቾችን ቁጥር እንዲያሻቅብ ከሚያደርጉ ተጨማሪ ምክንያቶች መካከል ተጠቅሰዋል።