ኔታንያሁ በአሜሪካ ድጋፍ "በኢራን የጀመርነው ፍጻሜውን ያገኛል" አሉ
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ጋር በእየሩሳሌም መክረዋል

ሮቢዮ "ሃማስ በሃይል ለማስተዳደር ሙከራ ካደረገ በጋዛ ሰላም ማስፈን የማይታሰብ ነው" ብለዋል
እስራኤልና አሜሪካ የኢራንን የኒዩክሌር የጦር መሳሪያ ባለቤት የመሆን ፍላጎት ለማክሰም በቁርጠኝነት እየሰሩ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኢስትሩ ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ጋር በእየሩሳሌም ከመከሩ በኋላ በጋራ በሰጡት መግለጫ፥ ሁለቱ ሀገራት ቴህራን በመካከለኛው ምስራቅ የምታደርገውን "ወረራ" ለማስቆም በትብብር እንደሚሰሩም ገልጸዋል።
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር በበርካታ ጉዳዮች መክረናል ያሉት ኔታንያሁ፥ ከሁሉም በላይ ኢራን ትኩረት ማግኘቷን አብራርተዋል።
"አያቶላዎቹ የኒዩክሌር የጦር መሳሪያ እንዳይኖራቸው ተስማምተናል፤ እስራኤልና አሜሪካ በኢራን የሚደቀን አደጋን በአንድነት ይመክታሉ" ሲሉም መናገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በበኩላቸው፥ "በእያንዳንዱ የሽብር ቡድን፣ በእያንዳንዱ ሁከትና አጥፊ እንቅስቃሴ፣ በቀጠናው የሚሊየኖችን ሰላምና ደህንነት አደጋ በሚጥል ተግባር ኢራን ከጀርባ አለች" ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ አስቀድመው የተናገሩትን "ኒዩክሌር የታጠቀች ኢራን አትኖርም" ሃሳብ በመድገምም አጽንኦት ሰጥተውታል።
ኔታንያሁ በመግለጫቸው ባለፉት 16 ወራት ኢራንና በቀጠናው የምታስታጥቃቸው ሃይሎች ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰባቸው አውስተዋል።
በደቡባዊ ሊባኖስ እና በሶሪያ በሚገኙ የሄዝቦላህ ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ የተፈጸሙ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአየር ጥቃቶች በቴህራን የሚደገፉ ቡድኖች በእስራኤል ላይ አዲስ ጥቃት እንዳይከፍቱ ማድረጉንም ነው ያብራሩት።
ሮቢዮን የእስራኤልን የጋዛ ፖሊሲ ያለምንም ጥርጣሬ በመደገፋቸው ያመሰገኑት ኔታንያሁ፥ እስራኤልና አሜሪካ በትራምፕ አስተዳደር በፍልስጤም ጉዳይ የጋራ አቋም መያዛቸውን ተናግረዋል።
ኔታንያሁ እና ሩቢዮ በመግለጫቸው በስፋት ባያነሱትም ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋዛን ለመጠቅለል ያቀረቡት እቅድ ዙሪያ ምክክር ተደርጓል።
"ፕሬዝዳንት ትራምፕ በጋዛ ቀጣይ እጣ ፈንታ ዙሪያ የያዙት እቅድ በርካቶችን ቢያስደነግጥም ከዚህ ቀደም ያልተሞከረ እና ጉልህ ለውጥ የሚያመጣ ነው" ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ።
በፍልስጤሙ ቡድን ሃማስ ዙሪያም የእስራኤልን አቋም እንደሚደግፉ ገልጸው "ሃማስ በሃይል ለማስተዳደር ሙከራ ካደረገ በጋዛ ሰላም ማስፈን የማይታሰብ ነው" ማለታቸው ተዘግቧል።
ሩቢዮ የቴል አቪቭ ቆይታቸውን ሲያጠናቅቁ ወደ ሳኡዲ አረቢያ እና አረብ ኤምሬትስ ያቀናሉ።
ሪያድ እና ሌሎች የአረብ ሀገራት የትራምፕን ፍልስጤማውያንን ከጋዛ የማፈናቀል እቅድ ማውገዛቸው የሚታወስ ነው።