![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/15/258-170743-whatsapp-image-2025-02-15-at-4.07.26-pm_700x400.jpeg)
ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሩሲያ እና ቻይና የአውሮፓ ደህንነት ስጋቶች አይደሉም ብለዋል
አዲሱ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ንግግር ለምን አውሮፓዊያንን አስደነገጠ?
የጀርመኗ ሙኒክ ከተማ ትኩረቱን በዓለም የጸጥታ እና ደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ ያደረገ ጉባኤ እያስተናገደች ነው፡፡
በዚህ ጉባኤ ላይ የሀገራት መሪዎች፣ ወታደራዊ ተቋማት መሪዎች እና ባለሙያዎችን ጨምሮ ሌሎች ተጋባዦች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉ የሀገራት መሪዎች ፍጹም የተራራቁ ሀሳቦችን ማንሳታቸው መድረኩ ከእስከዛሬ የተለየ አድርጎታል፡፡
የዩክሬን ጦርነት እና የጋዛ ሁኔታ የመድረኩ ዋነኛ ማጠንጠኛ እንደሚሆን ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም የአውሮፓ ጉዳይ ዋነኛ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡
በተለይም የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ጄዲ ቫንስ ያደረጉት ንግግር የጉባኤው አዘጋጅ ጀርመንን ጨምሮ የአውሮፓ ሀገራትን መሪዎች እንዳበሳጨ ተገልጿል፡፡
በመድረኩ ላይ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንደሚገኙ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም ሳይታሰብ ወጣቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ቫንስ ተገኝተው ሩሲያን እና ሌሎች የአውሮፓ ደህንነት ስጋት የተባሉ ሀገራትን ይኮንናሉ ተብለው ቢጠበቁም ተቃራኒውን አድርገዋል፡፡
“የአውሮፓ የደህንት ስጋት ምንጭ ሩሲያ አይደለችም፣ ቻይናም አይደለችም፣ የአውሮፓ ስጋት ራሱ አውሮፓ ነው” ብለዋል ቫንስ፡፡
እንደ ጄዲ ቫንስ አስተያየት ከሆነ በአውሮፓ ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ መሆኑ እና የስደተኞች ጉዳይ ለአውሮፓ ዲሞክራሲ ዋነኛ ስጋት ሆኗል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ምክትላቸው በሙኒክ ተገኝተው ያደረጉትን ንግግር ያደነቁ ሲሆን ለአውሮፓዊያን ጥሩ ማስጠንቀቂያ ነው ሲሉ አሞካሽተዋል፡፡
ዩክሬንን የኔቶ አባል ማድረግ የማይመስል ነገር ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሩሲያ የተያዙ የዩክሬን ግዛቶችን ማስመለስ የማይሳካ ነገር ነውም ብለዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን እና ጀርመን በበኩላቸው የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ንግግር ያልተጠበቀ እና ትክክለኛ ልሆነ ነው ሲሉ ውድቅ አድርገዋል፡፡
የህብረቱ ኮሚሽነር ኡርሱላ ቮንደርሊን የዩክሬን መሸነፍ ለአውሮፓ ስጋት መሆኑን ይህም የአሜሪካንን ጥቅም እንደሚጎዳ ተናግረዋል፡፡
የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር ቦሪስ ፒስቶሪየስ ካልተሳሳትኩ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ንግግር ስለ አውሮፓ ሳይሆን ስለ አምባገነን መሪዎችን የሚናገሩ ይመስላል ብለዋል፡፡