ዓለም አቀፉ የፊልም ኩባንያ በሶስት ወራት ውስጥ ከ9 ሚሊዮን በላይ አዲስ ደንበኛ ማግኘቱን አስታውቋል
ኔትፍሊክስ በትርፍ መንበሽበሹን አስታወቀ።
ፊልሞችን እና ዘጋቢ ፊልሞችን በመስራት የሚታወቀው ኔትፍሊክስ ኩባንያ ትርፉ እንደደራለት አስታውቋል።
እንደ ድርጅቱ ገለጻ ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ አግኝቻለሁ ብሏል።
ድርጅቱ አክሎም በተጠቀሱት ተመሳሳይ ወራት ውስጥ 9 ነጥብ 3 ሚሊዮን አዲስ ደንበኞችን በማግኘት የጠቅላላ ደንበኞቹ ቁጥር ወደ 270 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን አስታውቋል።
ድርጅቱ ያገኘው ትርፍ የ15 በመቶ እድገት እንዳሳየ ለኩባንያው ባለ አክስዮኖች የጻፈውን ደብዳቤ ዋቢ አድርጎ ቢቢሲ ዘግቧል።
ኔትፍሊክስ ኩባንያ በተያዘው 2024 ዓመት 9 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ለማትረፍ የያዘው እቅድ በጥሩ ሁኔታ እየሄደለት መሆኑን አስታውቋል።
የኩባንያው ፋይናንስ ሪፖርት ይፋ መደረጉን ተከትሎ የአክስዮን ዋጋው የ30 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል።
መሰረቱን አሜሪካ በማድረግ የተለያዩ ፊልሞችን ለተመልካቾች በማድረስ የሚታወቀው ኔትፍሊክስ ከዚህ በፊት ገቢው ማሽቆልቆሉን ተከትሎ የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዷል።
ኩባንያው ከወሰዳቸው እርምጃዎች ውስጥ የኔትፍሊክስ አካውንት ያላቸው ደንበኞች የይለፍ ቃላቸውን ለቤተሰቦቻቸው እንዲያጋሩ እና ፊልሞችን ማየት እንደሚችሉ የሚፈቅደውን አሰራር መተው ዋነኛው ነበር።
በዚህ እርምጃ ምክንያት ኩባንያው በደንበኞች ድርቅ እና ኪሳራ ይመታል ተብሎ ተገምቶ የነበረ ቢሆንም ግምቶቹ እስካሁን እንዳልሰሩ ተገልጿል።