የኢለን መስኩ ኒውራሊንክ በካናዳ አካል ጉዳተኞች ላይ ቺፕ ለመቅበር ፈቃድ አገኘ
በራስ ቅል ላይ የሚገጠመው ቺፕ በተለይም አካል ጉዳተኞች ወደ ቀድሞ ጤናቸው እንዲመለሱ የሚያደርግ ነው
በአሜሪካ ስራ ላይ የዋለው ኒውራሊንክ በሁለት አካል ጉዳተኞች ለይ ተሞክሮ ውጤታማ ሆኖ ተገኝቷል
የኢለን መስኩ ኒውራሊንክ በካናዳ አካል ጉዳተኞች ላይ ቺፕ ለመቅበር ፈቃድ አገኘ፡፡
የአሜሪካዊው ቢሊየነር ኢለን መስክ ንብረት የሆነው የባዮ ቴክኖሎጂ ኩባንያ ኒውራሊንክ ባለፈው ጥር ወር የመጀመሪያውን ችፕስ በሰው አእምሮ ውስጥ መቅበሩ ይታወሳል፡፡
የመስክ ባዮቴክ ኩባንያ የ30 አመት እድሜ ባለው ግለሰብ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ችፕ የገጠመው ባለፈው ጥር ወር ላይ ነበር።
ከዚህ በተጨማሪም ኩባንያው ባለፈው ነሀሴ ወር ሁለተኛውን ሙኩራ አሌክስ በሚል ስም ለሚጠራ አካል ጉዳተኛ አዕምሮ ውስጥ መግጠሙን እና ግለሰቡም ለውጥ በማሳየት ላይ እንደሆነ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።
ኩባንያው በሌላኛዋ የሰሜን አሜሪካ ሀገር ካናዳ አካል ጉዳተኞች ላይ እንዲሞከር ፈቃድ እንዳገኘ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
እንደዘገባው ከሆነ የካናዳ ጤና ዩንቨርሲቲዎች ማህበር የኒውራሊንኩን ቺፕ የመንቀሳቀስ ችግር ላጋጠማቸው ዜጎች መግጠም የሚያስችለውን ቀዶ ጥገና ህክምና ለማድረግ ዝግጁ ናቸው፡፡
በሰው አእምሮ ውስጥ የሚቀበሩ ቺፕሶች ወደፊት የእጅ ስልኮችን ይተካሉ- መስክ
የሳንቲም መጠን ያላትን ቺፕ የሰው ልጅን እንቅስቃሴ ፍላጎት ከሚያዘው የአእምሮ ክፍል ላይ በቀዶ ጥገና እንድትቀመጥ የሚደረግ ነው።
ይህቺ ቺፕ የአእምሮን እንቅስቃሴ በመመዝገብ እና የእንቅስቃሴ ፍላጎትን ወደሚተረጉም ማቀላጠፊያ መተግበሪያ ወይም አፕ ለማስተላለፍ ጥቅም ላይ ትውላለች።
ባሳለፍነው ነሀሴ በቀዶ ጥገና አማካኝነት ቺፕ የተገጠመለት እና በጀርባው ላይ በደረሰበት ጉዳት የእጅ እና እግር መገጣጠሚያ አጥንቶቹን ማንቀሳቀስ አይችልም የተባለው አሌክስ ይህች የኒውራሊንክ ችፕስ ከተገጠመችለት በኋላ በኮምፒውተር ጌም መጫወት ጀምሯል ተብሏል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ ግለሰቡ በተገጠመለት ቺፕ አማካኝነት አልታዘዝ ሲሉ የነበሩት የተወሰኑት ነርቮቹ መንቀሳቀስ ጀምረዋል፡፡
ኩባንያው እንዳለው በቀጣይ ቀስ በቀስ ነርቮቹ ሙሉ ለሙሉ እንዲታዘዙ ለማድረግ ማለማመዶች እና ተያያዥ ስራዎች ይሰራሉ ብሏል፡፡
ቺፑ የተገጠመለት አሌክስ በበኩሉ ለአዕምሬዬ ተስማሚ ቅርጽ ያላት ቺፕስ ከተገጠመልኝ ጊዜ ጀምሮ ህይወቴን እንደ አዲስ እየገነባሁ እንዳለሁ ይሰማኛል ሲል በወቅቱ ተናግሮ ነበር፡፡