የሰውነትዎትን እንቅስቃሴ በማየት ብቻ አነቃቂ ንግግሮችን ሳይቀር የሚያቀርበው አዲሱ የእጅ ሰዓት
በእጅ ጣት ላይ የሚደረገው ይህ ሰዓት ቡና መቼ መጠጣት እንዳለብዎትም ያስታውሳል
አዲሱ ሰዓት ከልብ ፣ማህጸን እና ሳምባ ጤና ባለፈ እንደ ኮቪድ መሰል ህመሞችን በራሱ ጊዜ ናሙና ወስዶ ውጤቱን ይናገራል
የሰውነትዎትን እንቅስቃሴ በማየት ብቻ አነቃቂ ንግግሮችን ሳይቀር የሚያቀርበው አዲሱ የእጅ ሰዓት
የአሜሪካዋ ላስ ቬጋስ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ በማስተናገድ ላይ ስትሆን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ለእይታ ቀርበዋል።
በዚህ አውደ ርዕይ ላይ ከቀረቡ ለየት ያሉ የቴክኖሎጂ ምርቶች ውስጥ በእጅ ጣቶች ላይ የሚደረገው ዘማናዊ ሰዓት ነው።
ይህ በጣት ላይ እንደ ቀለበት የሚደረገው ሰዓት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም ኤአይ ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙ ናቸው ተብሏል።
ሰዓቱ መሰረቱን ህንድ እና ዩኬ ባደረገው አልትራ ሂዩማን የተሰኘው ኩባንያ ከደቡብ ኮሪያው ናኖኢንቴክ ኩባንያ ጋር በጋራ እንደተሰራ ተገልጿል።
ዩሮ ኒውስ እንደዘገበው ከሆነ ጣት ላይ የሚደረገው ሰዓት የልብ፣ ሳምባ፣ ማህጸን እና ሌሎች የሰውነት ክፍሎች የጤና ሁኔታን ይከታተላል።
በተለይም ከስሜት ጋር በተያያዘ እንደ ድብርት፣ እንቅልፍ ማጣት፣ ጭንቀት እና መሰል ስሜቶችን ይቆጣጠራልም ተብሏል።
በሰውነታችን ውስጥ ያለውን የካፌይን መጠን በመለካት መቼ ቡና መጠጣት እንዳለብንም ይህ ሰዓት ያስታውሳል።
ከቆዳችን ውስጠኛ ክፍል ናሙናዎችን በራሱ በመውሰድ እንደ ኮቪድ አይነት ህመሞች እንዳለብን ያሳውቃልም ተብሏል።
ሰዓቱ በአጠቃላይ የሰውነታችንን እንቅስቃሴ በመመልከት አነቃቂ ንግግሮችን ሳይቀር በመናገር ስለ ራሳችን መልካም ነገር እንዲሰማን እንደሚያደርግም ተገልጿል።
እንዲሁም የጀመርናቸው መድሀኒቶች ካሉም መውሰድ ባለብን ሰዓት እንድንወስድ ማስታወስን ጨምሮ የተመገብናቸው ምግቦች ይዘትንም ሪፖርት ያደርጋል ተብሏል።
ኩባንያው ይህን ምርቱን በ130 ዶላር ለዓለም ገበያ እንደቀረበ ተገልጿል።