እስካሁን በጦርነቱ ከ700 በላይ ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል
አዲሱ የናጎርኖ-ካራባክ የተኩስ አቁም ስምምነት በሰዓታት ውስጥ ተጣሰ
በናጎርኖ-ካራባክ አካባቢ በተፈጠረው ግጭት አርመኒያ እና አዘርባጃን የደረሱት አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመጣሱ እርስ እየተወነጃጀሉ ነው፡፡
ስምምነቱ ትናንት ቅዳሜ የተደረሰ ቢሆንም የአርሜኒያ የመከላከያ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ሹሻን እስቴፓንያን በትዊተር ገፃቸው እንዳሉት አዘርባጃን የተኩስ አቁም ስምምነት ከተጀመረ ከደቂቃዎች በኋላ እሑድ ማለዳ ላይ የመሣሪያ ጥይት እና ሮኬቶችን መተኮሷን አስታውቀዋል፡፡
በስቴፓናከርት የተፈጸመውን ድብደባ ተከትሎ የህንፃ ፍርስራሾች- ላይ-ሮይተርስ
አዘርባጃን በተቃራኒው ለስምምነቱ መጣስ አርሜኒያን ተጠያቂ ታደርጋለች፡፡ የሀገሪቱ ፕሬስ ድርጅት እንደዘገበው በደቡብ ምዕራብ የጃብራይል ግዛት እንዲሁም በአራስ ወንዝ ዳርቻ በሚገኙ መንደሮች ላይ አርሜኒያ ከባድ መሳሪያዎችን ተኩሳለች፡፡
ዘ ናሺናል እንደዘገበው የቅዳሜው የተኩስ አቁም አዋጅ የወጣው ጦርነቱ በከፍተኛ መጠን መባባሱን እና በአዛርባጃን ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ ጋንጃ ውስጥ ሕፃናትን ጨምሮ 13 ሲቪሎችን የገደለ ሚሳኤል መተኮሱን ተከትሎ ነው፡፡ የአዘሪ ፕሬዝዳንት ኢልሀም አሊየቭ ለጥቃቱ የበቀል እርምጃ እንደሚወስዱ ዝተዋል፡፡
በጋንጃ ፣ አዘርባጃን ከተማ በሮኬት በተመታ የፍንዳታ ቦታ ላይ የነፍስ አድን ቡድኖች በስራ ላይ-ሮይተርስ
ተፋላሚ ወገኖች እስረኞችን እና የሟቾችን አስከሬን እንዲለዋወጡ እና ውይይቶችን እንዲጀምሩ ከሳምንት በፊት ባለፈው ቅዳሜ በሩሲያ የደረሱት የተኩስ አቁም ስምምነትም ወዲያው የተጣሰ ሲሆን ለስምምነቱ መጣስ ሁለቱም ወገኖች እርስ በእርስ ተወነጃጅለዋል፡፡
ካራባክ አካባቢን የተቆጣጠሩት የአርማኒያ ተገንጣዮች እና አዘርባጃን እ.ኤ.አ. በ 1990 ዎቹ 30,000 ሰዎች ከተገደሉበት ጊዜ አንስቶ በተራራማው አካባቢ ዕጣ ፈንታ ላይ ለመወሰን ሲጋጩ ቆይተዋል፡፡
ከሶስት ሳምንት በፊት ዳግም የተፈጠረው ግጭት እስካሁን ከ 700 በላይ ሰዎችን ለሞት ዳርጓል፡፡ ለአስርተ ዓመታት የዘለቀው ዓለም አቀፍ ሽምግልና አለመሳካቱን የተመለከትንበት ግጭቱ የቀጣናውን ኃያላን ሩሲያን እና ቱርክን በሰፊው አሳትፎ ወደ ቀጣናዊ ጦርነት እንዳያድግ ተሰግቷል፡፡
አዘርባጃን ከ60 ሰላማዊ ዜጎች ሞት ውጭ የወታደሮቿን የሞት ቁጥር አለማሳወቋን መነሻ በማድረግ እውነተኛው የሟቾች ቁጥር ከተጠቀሰው የበለጠ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡ የናጎርኖ-ካራባክ ባለስልጣናት በበኩላቸው 633 ወታደሮች እና 36 ንጹሃን በጦርነቱ መገደላቸውን አስታውቀዋል፡፡
በሁለቱም ወገኖች በኩል ወሳኝ የሚባል ድል ያገኘ አለመኖሩ እንዲሁምለሰላማዊ ድርድር እምብዛም ዝግጁ አለመሆናቸው ሲታይ ውጊያው መቼ ሊያቆም ይችላል ለሚለው ጥያቄ ምላሽ መስጠትን አዳጋች ያደርገዋል፡፡