ጥቃቱን ያደረሰው ግለሰብ የአይ ኤስ የሽበር ቡድን ባንዲራ ሲያውለበልብ ነበር ተብሏል
በአሜሪካ ኒውኦርሊያንስ በአንድ ስፍራ በተሰባሰቡ ሰዎች ላይ በመኪና ሆን ብሎ በተፈጸመ ጥቃት የሟቾች ቁጥር 15 መድረሱ ተነግሯል።
በርበን በተባለ ጎዳና አንድ ግለሰብ ፒካፕ መኪና በፍጥነት ሰዎች ላይ በመንዳትና በመግጨት ባደረሰው ጥቃት ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ ከ30 በላይ ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡
ጥቃቱ የተፈጸመው አዲስ አመትን በማክበር ላይ በሚገኙ የከተማዋ ነዋሪዎች እና ጎብኝዎች ላይ መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ጥቃቱን አድርሷል የተባለው ግለሰብ የአሜሪካ ጦር የቀድሞ አባል የነበረ እና ጥቃቱን ከማድረሱ ቀደም ብሎ የአይ ኤስ የሽበር ቡድን ባንዲራ ሲያውለበልብ ነበር ተብሏል።
የ42 ዓመት እድሜ ያለው ሸምሱድ ቢን ጃባር የተባው ጥቃት አድራሹ የአሜሪካ ዜግት ያለው የቴክሳስ ነዋሪ ሲሆን፤ የአሜሪካ ጦር አባል በመሆን በአፍጋስን ውስጥ ማገልግሉም ተነግሯል።
ከጥቃቱ በኋላ ሸምሱድ ቢን ጃባር በፖሊስ በተተኮሰበት ጥይት ጥቃቱን በፈጸመበት በደረሰበት ስፍራ አቅራቢያ መገደሉም ነው የተነገረው።
የአሜሪካ የፌደራል የምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ጃባር ከሽብርተኛ ቡድኖች ጋር ምን ግንኙነት ነበረው የሚለውን እየመረመረ እንደሆነ አስታውቋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን "አስጸያፊ" ያሉትን ጥቃት አውግዘው በጥቃቱ ዙሪያ ምርመራዎች መቀጠላቸውን አስታውቀዋል።
ባይደን አከለውም፤ መርማሪዎች በላስ ቬጋስ ከትራምፕ ሆቴል በር ላይ ከቴስላ ተሽከርካሪ ቃጠሎ ጋር ግንኙነት ሊኖር ወይም አለመኖሩን እየመረመሩ ነው ብለዋል።
እስካሁን ድረስ ሁለቱን ክስተቶች የሚያገናኝ ምንም አይነት ማስረጃ የለም ሲል ባይደን ተናግረዋል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መሰል በመኪና የሚፈጸሙ ጥቃቶች እየተበራከቱ ይገኛሉ፤ በቻይና ብቻ በስፖርት ማዕከል እና በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ በተፈጸመ ሁለት ጥቃት በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፡፡
በሌላ በኩል በጀርምን በገና በአል ሸመታ ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ አንድ የ50 አመት ግለሰብ ባደረሰው ጥቃት 8 ሰዎች ሲገደሉ ከ200 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
የቻይናውን ሁለት ጥቃቶች ጨምሮ በቅርብ ጊዜ ተመሳሳይ የመኪና ጥቃቶች ሲፈጸሙ ይህ ለአራተኛ ጊዜ ነው፡፡