በአሜሪካ ኒውኦርሊያንስ አንድ ግለሰብ በመኪና ባደረሰው ጥቃት አስር ሰዎች ሞቱ
ግለሰቡ አዲስ አመትን ለማክበር በተሰባሰቡ ሰዎች ላይ መኪና በመንዳት ባደረሰው ጥቃት 35 ሰዎች ቆስለዋል
በቅርብ ጊዜ ከቻይና እና ጀርመን ቀጥሎ መሰል ጥቃት ሲፈጸም ይህ ለአራተኛ ጊዜ ነው
በአሜሪካ ኒውኦርሊያንስ አንድ ግለሰብ በመኪና ሆን ብሎ ባደረሰው ጥቃት አስር ሰዎችን መግደሉ ተዘግቧል፡፡
በርበን በተባለ ጎዳና ግለሰቡ የፒካፕ መኪና በፍጥነት በማሽከርከር ባደረሰው ጥቃት ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ 35 ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡
ጥቃቱ የተፈጸመው አዲስ አመትን በማክበር ላይ በሚገኙ የከተማዋ ነዋሪዎች እና ጎብኝዎች ላይ መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ግለሰቡ ከተሽከርካሪው ላይ እያለ በፖሊሶች ላይ በከፈተው ተኩስ ሁለት ፖሊሶችን ማቁሰሉን እና ጥቃቱ እንደ ሽብር ተግባር እየተመረመረ መሆኑን የአሜሪካ የፌደራል የወንጀል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) አስታውቋል፡፡
ከጥቃቱ በኋላ ግለሰቡ በፖሊስ በተተኮሰበት ጥይት አደጋው በደረሰበት ስፍራ አቅራቢያ መገደሉም ነው የተነገረው።
በርበን የተባለው ጎዳና በከተማዋ ሙዚቃ እና የምሽት ክለቦችን ፈልገው በሚመጡ ቱሪስቶች እና የከተማው ሰዎች መደረሻ ስለመሆኑ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
እስካሁን ስለግለሰቡ ማንነት እና ጥቃቱን ስላደረሰበት ምክንያት ባይታወቅም አደጋው በደረሰበት አካባቢ አቅራቢያ ተቀጣጣይ ፈንጆች መገኘታቸውን ተከትሎ ፖሊስ ነዋሪዎች በቤታቸው እንዲቆዩ አስጠንቅቋል፡፡
በስፍራው የነበሩ የአይን እማኞች አጋጣሚውን በጭካኔ የተሞላ እና በየስፍራው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ወድቀው በስቃይ ሲያቃስቱ መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መሰል በመኪና የሚፈጸሙ ጥቃቶች እየተበራከቱ ይገኛሉ፤ በቻይና ብቻ በስፖርት ማዕከል እና በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ በተፈጸመ ሁለት ጥቃት በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፡፡
በሌላ በኩል በጀርምን በገና በአል ሸመታ ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ አንድ የ50 አመት ግለሰብ ባደረሰው ጥቃት 8 ሰዎች ሲገደሉ ከ200 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው የሚታወስ ነው፡፡
የቻይናውን ሁለት ጥቃቶች ጨምሮ በቅርብ ጊዜ ተመሳሳይ የመኪና ጥቃቶች ሲፈጸሙ ይህ ለአራተኛ ጊዜ ነው፡፡