በአሜሪካ ብቅ ያለው አዲሱ የ“ፎርዎርድ” ፓርቲ ዴሞክራቶችን እና ሪፐብሊካን ፓርቲዎች ስጋት ውስጥ ከቷል ተባለ
“ፎርዎርድ ፓርቲ” በቀድሞው የዲሞክራቲክ ፕሬዚዳንታዊ እጩ አንድሪው ያንግ እና የኒው ጀርሲ ሪፐብሊካን ገዢ ክሪስቲን ቶድ ዊትማን የመመራ ነው
ሁለት ሶስተኛው አሜሪካውያን ሶስተኛ ወገን እንደሚፈልጉ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡
በአሜሪካ ምድር ብቅ ያለው አዲሱ የ“ፎርዎርድ” ፓርቲ ዴሞክራቶችን እና ሪፐብሊካን ፓርቲዎች ስጋት ውስጥ መክተቱ ተገለጸ፡፡
አዲሱ ፓርቲ በደርዘን በሚቆጠሩ የቀድሞ የሪፐብሊካን እና የዲሞክራቲክ ባለስልጣናት አማካኝነት የተመሰረተ ሲሆን ለአሜሪካውያን አዳዲስ የፖሊሲ አማራጮች ይዞ እንደሚመጣ ይጠበቃል፡፡
ሮይተርስ እንደዘገበው፤ አዲሱ ፓርቲ በአሜሪካ ረዥም ዘመናት ባስቆጠሩ ሁለቱም የሪፐብሊካን እና የዲሞክራቲክ ፓርቲዎች "ያልተሰሩ" ስራዎች ለመስራት አቅዶ የተነሳና በዚህም የሚሊዮን አሜሪካውያን ልብ የማሸነፍ የሚፈልግ ነው፡፡
“ፎርዎርድ” ወይም “ወደፊት” ተብሎ የሚጠራው አዲሱ ፓርቲ በቀድሞው የዲሞክራቲክ ፕሬዚዳንታዊ እጩ አንድሪው ያንግ እና በቀድሞው የኒው ጀርሲ ሪፐብሊካን ገዢ ክሪስቲን ቶድ ዊትማን የመመራ ነው።
አዲሱ ፓርቲ በ2021 በሮናልድ ሬጋን ፣ በጆርጅ ኤች ቡሽ ፣ በጆርጅ ደብልዩ ቡሽ እና በዶናልድ ትራምፕ የሪፐብሊካን አስተዳደሮች ዘመን በደርዘን የሚቆጠሩ የቀድሞ ባለስልጣናት የተቋቋመውን የታደሰው አሜሪካ ንቅናቄን ያጠቃልላልም ነው የተባለው፡፡
መስራች አባላቱ ፓርቲው የአሜሪካን ፖለቲካ ከሚቆጣጠሩት የሪፐብሊካን እና የዴሞክራቲክ ፓርቲዎች የተሻለ አማራጭ ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
በዚህም የፓርቲው መሪዎች መድረኩን ለህዝብ ለማስተዋወቅና ድጋፍ ለመሳብ በያዝነው አመት ከ20 በሚበልጡ ከተሞች ተከታታይ ኮንፈረንሶችን ያደርጋሉ ተብሏል።
በተጨማሪም በመስከረም 24 የአሜሪካ ትልቅ ከተማ በሆነችው በሂዩስተን ውስጥ የፓርቲው የመጀመሪያ ሀገር አቀፍ ጉባኤ የሚያካሂድ ይሆናል፡፡
ሁለት ሶስተኛው አሜሪካውያን ሶስተኛ ወገን (አማራጭ ሃሳብ ያለው አዲስ ፓርቲ) እንደሚፈልጉ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡
“ፍትሃዊ እና የበለጸገ ኢኮኖሚን ሪፎርም ማድረግ” እንዲሁም “አሜሪካውያን በምርጫ ብዙ አማራጭ እንዲኖራቸጉ፣ በሚሰራ መንግስት ላይ የበለጠ እምነት እንዲኖራቸው እና በወደፊታችን ላይ የበለጠ የመናገርበት ሁኔታ እንዲኖር” የሚሉ አንኳር ጉዳዮች የአዲሱ ፓርቲ ዋና ዋና ምሰሶዎች እንደሆኑም ተገልጿል።
ሆኖም አዲሱ ፓርቲ ከነባር ፓርቲዎች የሚለይባቸው ፖሊሲዎች ላይ እንስካሁን በግልጽ ያለው ነገር የለም፡፡