ተመራማሪዎች ልክ እንደተክሎች ካርቦንን ከከባቢ አየር ላይ የሚሰበስብ ፈጠራ አስተዋወቁ
አዲሱ የፈጠራ ግኝት ከአየር ላይ የሰበሰበውን አየር ለፋብሪካዎች አገልግሎት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ነው
የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ቴክኖሎጂዎች አስፈላጊ ቢሆኑም ተፈጥሯዊ መፍትሄዎችም እንዳይዘነጉ ተመራማሪዎች አስጠንቅቀዋል
የአሜሪካ ተመራማሪዎች ልክ እንደ ዛፍ እና ተክሎች ከከባቢ አየር ላይ ካርቦንዳይኦካሳይድን የሚሰበስብ ዱቄት (ፓውደር) ማግኝታቸውን አስታውቀዋል።
በቤተ ሙከራ ውስጥ የተፈጠረው ቢጫ ቀለም ያለው ዱቄት ለአየር ንብረት ለውጥ እና ለተፈጥሮ አደጋ መባባስ ምክንያት የሆነውን የካርቦን ጋዝን በመሰብሰብ የአየር ንብረት ተጽዕኖን ለመቋቋም ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው ተብሏል።
በቅድመ ሙከራዎች መሰረት ግማሽ ፓውንድ ወይም 226.7 ግራም ዱቄት የአንድን ዛፉ ያህል ካርቦን ዳይኦክሳይድ የማስወገድ አቅም ያለው ሲሆን የተሰበሰበው ካርበን ወደ ደህንነቱ የተጠበቀ ማከማቻ ውስጥ በማስቀመጥ ለኢንዱስትሪ አገልግሎት ይውላል ነው የተባለው።
በካሊፎርኒያ በርክሌይ ዩኒቨርሲቲ የኬሚስትሪ ተመራማሪው ኦማር ያጊ “ይህ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ከመከላከል ጋር በተገናኝ በቴክኖሎጂ መስክ ያለውን ትልቅ ችግር የሚፈታ ነው ፤አሁን የዚህን ዱቄት ምርት በመጨመር በሰፊው መጠቀም እንድንጀምር እድል ይሰጠናል” ብለዋል።
ተመራማሪው ከኃይል ማመንጫዎች ወይም ከከተሞች ከባቢ አየር ላይ በካይ ጋዞችን ለመሰብሰብ የሚያስችሉ ተመሳሳይ ግኝቶችን ለማስተዋወቅ ለበርካታ አስርተ ዓመታት በምርምር ላይ የቆዩ መሆናቸውን ዘጋርዲያን አስነብቧል።
“ኮቫለንት ኦርጋኒክ ፍሬምወርክ” የተሰኝ ስያሜ የተሰጠው ፓውደር ጋዞችን ከአየር ውስጥ የሚስቡ ጠንካራ ኬሚካሎችን በውስጡ የያዘ ነው።
ከአንድ ጊዜ በላይ ጥቅም መስጠት መቻሉ እና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ መሆኑ ከዚህ ቀደም የካርቦን ጋዝን ለመያዝ አገልግሎት ከሚሰጡ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሚለየው እንደሆነም ነው የተመላከተው።
የግኝቱ ባለቤት ያጊ እና ባልደረቦቻቸው በቤተ ሙከራ ውስጥ አዲሱ ዱቄት በተሳካ ሁኔታ ከ 100 ጊዜ በላይ የካርቦን ጋዝን መሰብሰብ እና መልቀቅ እንደሚችል አረጋግጠዋል።
ዱቄቱ ቀዳዳ በተበጀላቸው ብልቃጦች ውስጥ ካርበን በሚበዛባቸው ስፍራዎች ላይ ከተቀመጠ በኋላ በሁለት ሰአታት ውስጥ በካርበን ይሞላል ቀጥሎም ድጋሚ ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት በ120 ዲግሪ ፋራናይት ሙቀት ውስጥ የሰበሰበውን ካርበን ወደ ማከማቻ ውስጥ እንዲለቅ ይደረጋል።
በቀጣይ ከአንድ አመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በበርካታ ቶን ምርት በማምረት ይህን አዲስ ቴክኖሎጂ በሰፊው ጥቅም ላይ ለማዋል እቅድ ተይዟል።
በጥናቱ ላይ ያልተሳተፉ ተመራማሪዎች በረዥም ጊዜ ውስጥ የአለም ሙቀት መጨመር ተጽእኖዎች እየጠነከሩ በሚገኙበት ወቅት ካርቦን ዳይኦክሳይድን ከከባቢ አየር የሚያስወግዱ ቴክኖሎጂዎች ፈጠራ ላይ ተጨማሪ ምርምሮች እንደሚያስፈልጉ ተናግረዋል።
ነገር ግን የአካባቢ መራቆትን መከላከል ፣ ችግኞችን መትከል እና ሌሎችም ተፈጥሯዊ የሆኑት የመፍትሄ መንገዶች ችላ ሊባሉ እንደማይገባ እስጠንቅቀዋል።
ከዚህ ባለፈም የድንጋይ ከሰል የሀይል አማራጮችን በታዳሽ ሀይሎች በመተካት የአለም ሙቀት መጠን መጨመርን መቀነስ እንደሚገባም አሳስበዋል።