የአውሮፓ ህብረት በቅርቡ በኢትዮጵያ ላይ ጣለው የቪዛ መጠየቂያ ገደብ ዙሪያ የሁለትዮሽ ውይይቶች እንደቀጠሉ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል
አዲሱ የንብረት ማስመለስ ረቂቅ ህግ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ዲያስፖራዎችን ይጎዳል?
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ በወቅታዊ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
አምባሳደር ነብዩ በመግለጫው ወቅት ከተነሱላቸው ጥያቄዎች መካከል ባሳለፍነው ሳምንት ይፋ ስለተደረገው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ ህግ አንዱ ነበር።
ይህ ረቂቅ ህግ በተለይም በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ላይ ስጋት መደቀኑን፣ ኢትዮጵያ በውጭ ከሚኖሩ ዜጎቿ ጋር ያላትን ግንኙነት ሊጎዳ አይችልም? እና ዲያስፖራዎችን ኢላማ ያደረገ ይመስላል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ አምባሳደር ነብዩ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል።
"ህጉ ገና በረቂቅ ደረጃ ላይ ነው፣ እንደ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር እኛም ገና አላየነውም፣ ረቂቅ ህጉ ከዲያስፖራዎች ጋር በተመለከት ጉዳት ካለው አስተያየት የምንሰጥበት ይሆናል" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ሪፖርተር ጋዜጣ አማርኛው ክፍል ባሳለፍነው እሁድ ይዞት በወጣው ዘገባ የንብረት ማስመለስ ረቂቅ ህግ ወደኋላ 10 ዓመት ድረስ በመሄድ አንድ ሰው ከሚታወቀው መደበኛ ህይወቱ በተለየ ንብረት ካፈራ ንብረቱን በህጋዊ መንገድ ስለማግኘቱ ለፍርድ ቤት እንዲያስረዳ ይገደዳል።
እንዲሁም ንብረቱ በህጋዊ መንገድ ስለመፈራቱ የሚያስረዳ ማስረጃ ካልተገኘ መንግሥት ንብረቱን የመውረስ መብት እንደሚሰጠው በረቂቅ ህጉ ላይ መቀመጡን በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ሌላኛው በዛሬው መግለጫ ላይ የተነሳው ጉዳይ በኢትዮጵያ ስለተጠለሉ ሱዳናዊያን ስደተኞች ከፍተኛ የደህንነት ስጋት እንደተደቀነባቸው እና ኢትዮጵያ ተገቢውን ጥበቃ እና ድጋፍ አላደረገችም የሚለው ጉዳይ ሲሆን የተሻለ ደህንነት ፍለጋ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሱዳናዊያንን ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ የክልል እና ፌደራል መንግስታት የተቀናጀ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በተለያዩ የሰብዓዊ ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞችን ደህንነት አላስጠበቀችም በሚል ከሰሞኑ የተለያዩ ተቋማት ባወጧቸው ሪፖርቶች ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጡም ለአምባሳደር ነብዩ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር።
ቃል አቀባዩም በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተሰማሩ ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች የሚሰሩ ሰራተኞችን ደህንነት እየጠበቀች መሆኗን ነገር ግን ከሰሞኑ በዚህ ዙሪያ የወጡ ሪፖርቶችን እንዳላዩ ተናግረዋል።
የአውሮፓ ህብረት በቅርቡ ኢትዮጵያን በሚመለከት ባወጣው የቪዛ ገደብ ዙሪያ ውይይት እየተደረገ መሆኑን፣ የመኖሪያ ቪዛ ያላገኙ በአውሮፓ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን የማጣራቱ ስራ እና ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ውይይቶች እንደቀጠሉ መሆኑንም አምባሳደር ነብዩ በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል።