የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስለፌልትማን ከስልጣን መልቀቅ እስካሁን በይፋ ያለው ነገር የለም
ነገ አዲስ አበባ ይመጣሉ ተብሎ የሚጠበቁት በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ከሃላፊነታቸው ሊለቁ ነው ተባለ፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ተደጋጋሚ ጉዞዎችን ያደረጉት ፌልት ማን ከዘጠኝ ወራት የስልጣን ቆይታ በኋላ እንደሚለቁ ነው ሮይተርስ የዘገበው፡፡ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን በነገው እለት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ይመክራሉ ቢባልም ዛሬ ስልጣን እንደሚለቁ ይፋ ተደርጓል፡፡ ሮይተርስ ይህንን ይበል እንጅ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ግን በጉዳዩ ላይ አስተያየት አልሰጠም ተብሏል፡፡
ጄፍሪ ፌልትማን በኢትዮጵያ ጉዳይ ለመምከር ግብፅ፣ ዩኤኢ እና ቱርክ መጓዛቸው የሚታወስ ሲሆን እርሳቸውን ይተኳቸዋል ተብለው የሚጠበቁት ደግሞ በቱርክ የአሜሪካ አምባሳደርነት ጊዜያቸውን የጨረሱት ዲፕሎማት ናቸው፡፡
ዲፕሎማቱ ዴቪድ ሰተርፊልድ በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ በመሆን ተሰናባቹን ጄፍሪ ፌልትማን እንደሚተኩ ለጉዳዩ ቅርብ ናቸው የተባሉ የዲፕሎማቲክ ምንጮች ተናግረዋል ተብሏል፡፡ ትናንና የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ፌልትማን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚጓዙ አስታውቀው ነበር፡፡
ፌልትማን በኢትዮጵያ ጦርነት እንዲሁም በሱዳን መፈንቅለ መንግስት ዙሪያ በተደጋጋሚ ወደ አፍሪካ ቀንድ መምጣታቸው የሚታወስ ሲሆን ለሁለቱም ችግሮች እልባት እንዳልሰጡ ይነገራል፡፡ፌልትማን ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ ተብሎ የነበረው በኢትዮጵያ ያለው ግጭት ሰላማዊ መፍትሄ እንዲያገኝ ለመነጋገር መሆኑን ሮይተርስ አንድ ከፍተኛ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባለስልጣንን ጠቅሶ ትናንት ዘግቦ ነበር፡፡
በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁት ሳተርፊልድ ከ 40 ዓመት በላይ የውጭ ግንኙነት ልምድ አላቸው፡፡ አዲሱ መልዕክተኛ ከዚህ በፊት በቱርክ፣ በሳዑዲ አረቢያ፣ በሊባኖስ፣ ቱኒዚያ እና ሶሪያ ያገለገሉ ሲሆን በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች ተጠባባቂ ኃላፊም በመሆን ሰርተዋል ተብሏል፡፡
አሜሪካ ግጭቱን በመተመለከተ የያዘችው አቋም በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ተቀባይት አላገኘም፡፡ አሜሪካ በኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጽሟል በተባለው የሰብአዊ መብት ጥስት ምክንያት ኢትዮጵያን ከቀረጽና ኮታ ነጻ የንግድ ችሮታ(አጎአ) የንግድ ትስስር መዘረዟ ይታወቃል፡፡
የአሜሪካ መንግስትን ወሳኔ የተቃወመችው ኢትዮጵያ፤ውሳኔው እንዲቀለበስ መጠየቋ ይታወሳል፡፡ ነገረግን እስካሁን በአሜሪካ በኩል የአቋም ለውጥ አልተሰማም፡፡
የኢትዮጵያ መንግሰት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካውጀና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ግንባር ከዘመቱ በኋላ በህወሃት ተይዘው የነበሩ በርካታ የአማራ እና የአፋር ክልል ቦታዎች ነጻ ወጥተዋል፡፡ መንግስት የህወሓት ሀይሎችን በማሸነፍ ይዘዋቸው ከነበሩ ቦታዎች እንዲወጡ ማድረጉን ሲገልጽ ህወሓት በአንጻሩ “ለሰላም እድል ለመስጠት” ሲባል ከአማራ እና አፋር ክልሎች ተዋጊዎቹን ማስወጣቱን ይገልጻል፡፡
ከአንድ አመት በላይ ያስቆጠረው ጦርነቱ በሺዎች ሲገደሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለው ህይወታቸው ተመሰቃቅሏል፡፡