ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጋር መነጋገራቸው ተሰማ
ተሰናባቹ ልዩ መልዕክተኛ ፌልትማን የመጨረሻ የልዩ መልዕክተኛነት ጉዟቸውን ወደ ኢትዮጵያ ያርጋሉ ተብሎ እንደነበር ይታወሳል
ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጄፍሪ ፌልትማን ጋር ምን እንዳወሩ በውል የተገለጸ ነገር የለም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ጋር ትናንት ሃሙስ ማውራታቸው ተሰማ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ፌልትማን መነጋገራቸውን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሆኖም ሚኒስቴሩ ትናንት ሃሙስ እንደተነጋገሩ ከመግለጽ ውጪ በምን ዐይነት መንገድ ተነጋገሩ በስልክ ወይስ በአካል ስለሚለው የገለጸው ነገር የለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም ሆኑ ጽህፈት ቤታቸው ስለጉዳዩ ያሉትም ነገር የለም፡፡
ንግግሩን ተከትሎ በተለይ ዓመት ያስቆጠረውን ጦርነት በተመለከተ የሚገኙ አዎንታዊ ነገሮች ይኖራሉ በሚል አሜሪካ ተስፋ ማድረጓን ሮይተርስ ሚኒስቴሩን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡
ተሰናባቹ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን የመጨረሻ የልዩ መልዕክተኛነት ጉዟቸውን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚያደርጉ ከሰሞኑ ተገልጾ ነበር፡፡ ትናንት ሃሙስ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር እንደሚመክሩ ነበር ሲጠበቅ የነበረው፡፡ ነገር ግን የተባለው እውን ስለመሆኑ የተረጋገጠ ነገር የለም፡፡
ከ8 ወራት በፊት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ስራ የጀመሩት አምባሳደር ፌልትማን ከአሁን ቀደም ኢትዮጵያን ጨምሮ በሱዳንና በሌሎችም የቀጣናው ሃገራት ጉብኝት አድርገዋል፡፡
በአዲስ አበባ በነበራቸው ቆይታ ግጭቱንና ሌሎች ጉዳዮችን በማስመልከት ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር መክረው እንደነበርም ይታወሳል፡፡
አሁን ግን በኃላፊነት የሚዘልቁበት ጊዜ ማብቃቱን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል። በቱርክ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ዴቪድ ሳተርፊልድ ከአሁን በኋላ ፌልትማንን ተክተው በአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛነት እንደሚሰሩም ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን ያስታወቁት፡፡
በቀጣናው ያለው አለመረጋጋት፣ ብጥብጥ፣ ሰብዓዊ ድቀት እና ሌሎች ፖለቲካዊ እና ስትራቴጂካዊ ሁነቶች አሜሪካ ዐይኗን እንድትነቅል የሚያደርጉ አይደሉም፡፡ ቀዳሚ ትኩረት ሰጥታ መቀጠልም ትፈልጋለች፡፡
ለዚህም ቀውስ በናጣቸው ሃገራት ጭምር የዳበረው የአምባሳደር ሳተርፊልድ አስርት ዓመታትን የተሻገረ ዲፕሎማሲያዊ ልምድ በቀንዱ አካባቢም ያስፈልጋል እንደ አንቶኒዮ ብሊንከን ገለጻ፡፡