ትራምፕ ሆቴላቸውን በ375 ሚሊዮን ዶላር ሊሸጡት ነው ተብሏል
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዋሸንግተን ዲሲ የሚገኘውንና በስማቸው የተሰየመውን ባለ ኮኮብ ቅንጡ ሆቴል ሊሸጡ መሆኑ ተገለጸ፡፡
ድርጅታቸው ትራምፕ ኢንተርናሽናል ሆቴልን በ375 ሚሊዮን ዶላር ለመሸጥ ከስምምነት ላይ መድረሱን ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
ዎል ስትሪት ጆርናል ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ሰዎች በመጥቀስ ትናንት እሁድ እንደዘገበው ከሆነ መቀመጫውን ማያሚ ያደረገና ሲ.ጂ.አይ የተባለ የኢንቨስትመንት ድርጅት በፔንስልቬንያ ጎዳና ላይ የሚገኘውን ትራምፕ ሆቴልን ለመግዛት ከትራምፕ ድርጅት ጋር የሊዝ ስምምነት ላይ ደርሷል።
ሲ.ጂ.አይ የሆቴሉ ስም ተቀይሮ ‘ዋልዶርፍ አስቶሪያ’ በተሰኘው የሂልተን የባለ ኮኮብ ሆቴሎች አስተዳደር ቡድን እንዲተዳደር ለማድረግ መስማማቱንም የመረጃ ምንጮቹ ለዎል ስትሪት ተናግረዋል፡፡
የግዥ ሂደቱ እስከ መጭው መጋቢት ድረስ እንደሚጠናቀቅም ነው ዘገባዎች ያመለከቱት፡፡
ትራምፕ ይሄንን ሆቴል በፈረንጆቹ በ2012 ዓመት የገነቡት ሲሆን ፕሬዘዳንት ሆነው እንደተመረጡ ይሸጡታል የሚሉ ሀሳቦች ቢነሱም ጥያቄውን ውድቅ አድርገውት ነበር፡፡
ይሁንና የቀድሞው ፕሬዝዳንት በ2019 ዓመት በ500 ሚሊዮን ዶላር ለመሸጥ ቢፈልጉም ገዢ በመጥፋቱ እስካሁን ቆይቷል ተብሏል፡፡
ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በነበሩበት ጊዜ የውጭ አገራት መሪዎች ወደ አሜሪካ ሲመጡ በሆቴላቸው እንዲያርፉ የተለያዩ ጫናዎችን በማድረግ እስከ 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝተዋል የሚሉ ትችቶች ይቀርቡባቸው ነበር፡፡
ይሁንና ቆይቶ በወጣ ሪፖርት ደግሞ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በሆኑባቸው አራት ዓመታት ውስጥ 70 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማጣታቸው ተገልጿል፡፡