እርምጃው የተወሰደው በግብጽ ቅንጡ ባቡሮች ውስጥ አይጦች መኖራቸውን የሚያሳይ የቪዲዮ መለቀቁን ተከትሎ ነው
አንድ የግብጽ ከፍተኛ የስራ ኃለፊ በአይጥ ምክንያት ከስራ ገበታቸው መባረራቸው ተነግሯል።
የግብፅ የትራንስፖርት ሚኒስትር ካሜል አል ዋዚር የሀገሪቱን የባቡር ኩባንያ የተቀናጀ አገልግሎት፣ የጽዳት እና የአስተዳደር መድህን ፕሬዚዳንት ኢንጅነር ሳሚ አብደል ተዋብን ነው ከሰልጣን ያነሱት።
ባለስልጣኑ ከስራቸው የተሰናበቱት በሩሲያ ሰራሽ ቅንጡ ባቡሮች ውስጥ አይጦች በመገኘታቸው ነው ተብሏል።
ካይሮ 24 ኒውስ የተባለ ድረ ገጽ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ምንጮችን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው፤ ኃፊው ከሰልጣናቸው እንዲነሱ ውሳኔ የተላለፈው ባሳለፍነው ማክሰኞ ነው።
እርምጃው የተወሰደውም በሩሲያ ሰራሽ ቅንጡ ባቡሮች ውስጥ አይጦች እንዳሉ የሚያሳይ የቅሬታ ቪዲዮ መለቀቁን ተከትሎ እንደሆነም ተነግሯል።
በዚህም ባቡሩ ውስጥ በሩሲያ ሰራሽ ባቡሮች ውስጥ ውስጥ ደካማ ንፅህና እና ደህንነት በመኖሩ ባለስልጣኑ ከኃላፊነታቸው ተባረዋል።
በሉክሶር- ካይሮ የባቡር መስመር ውስጥ አይጦች መኖራቸውን ተሳፋሪዎች ቅሬታ ማቅረባቸውንም ምንጮቹ አስታውቀዋል።
አይጦች ከአንድ በላይ ባቡር ውስጥ ታይተዋል የተባለ ሲሆን፤ ይህም በተሳፋሪዎች ላይ ድንጋጤ እና ቅሬታ የፈጠረ መሆኑንም ተናግረዋል።
እንደ ምንጮቹ ገለፃ ውሳኔው ከዛሬ ሀሙስ ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን፤ ሜጀር ጀነራል ሀተም ኢብራሂም የባቡር ኩባንያውን ለአንድ ዓመት እንዲመሩ ተሹመዋል።